“ፈተናውን በጽናት እና በማስተዋል የሚሻገር መሪ፤ ሀገርንም ሕዝብንም ማሻገር ይችላል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

27

ጎንደር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሔደ ነው። በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ችግር ማጋጠሙን አስታውሰዋል፡፡ ፈተናውን በጽናት እና በማስተዋል የሚሻገር መሪ ካለ ሀገርንም ሕዝብንም ማሻገር እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት፡፡

“የተንከባለሉ ሥራዎችን ለመፈጸም መሪዎች ከፍ ባለ ኀላፊነት የሥራ አፈጻጸሞችን መገምገም እና ለቀጣይ ዓመት መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። ተስፋ እና ጽናት ያለው መሪ ሕዝብን ያሻግራል ያሉት አቶ ደሳለኝ ለ2017 በጀት ዓመት ሁሉን አቀፍ ዕቅድ በክልል ደረጃ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት የልማት ዕቅድ ማቀዱን ገልጸው ከዚህ ዕቅድ ለ2017 የተመጠነው ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል። በመድረኩ የ2016 የፖለቲካ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ተግባራት አፈጻጸም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚመከር የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የዞኑ መሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበራ ገልጸዋል።

በ2016 ዓ.ም በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ከማስተካከል አኳያ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በአንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጠው የነበሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማስጀመር እንደተቻለ ተናግረዋል።
ከችግሩ ለመውጣት በአመለካከት እና በተግባር ፈርሶ የነበረውን የፖለቲካ እና የጸጥታ መዋቅር እንደገና የማሠባሠብ፣ የማጥራት፣ የማደራጀት እንዲሁም በሥነ ልቦና የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ከጸጥታ ሥራው ጋር ተሳስረው እንዲሠሩ መደረጉን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አላምረው ገለጻ ከአለፋ እና ጣቁሣ ወረዳዎች ውስን ትምህርት ቤቶች ውጭ ሌሎቹ በመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል። ሃሳባቸውን የሰጡን የውይይቱ ተሳታፊዎች በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአገልግሎት ዘርፎች በ2016 በጀት ዓመት በየወረዳቸው ጥሩ አፈጻጸም መከናወኑን አስገንዝበዋል።

ከማኅበረሰቡ እርካታ አኳያ የጎደሉትን በሚቀጥለው በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ነው ያብራሩት፡፡ በሌላ በኩል አዲሱን የክልሉ መንግሥት ዕቅዶች ለመተግበር ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የፍትሕ፣ የመልካም አሥተዳደር መስፈን፣ የሰላም እጦቶች እና የመሠረተ ልማት መጓደሎች አሁንም እንደሚስተዋሉ እና በአዲሱ በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሠሩባቸውም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ተስፋዬ አይጠገብ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ39 ሺህ በላይ ማሳ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሲስተም ውስጥ በማስገባት የመሬት ግብይት ተፈጽሟል” የደቡብ ወሎ ዞን መሬት መምሪያ
Next article“በትምህርቱ ዘርፍ የገጠመንን ስብራት ለመጠገን በጋራ እና በትብብር መሥራት ይኖርብናል ” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን