“የብርሃን መውጫ፤ የምስጢር መገለጫ”

65

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተቀደሰች ተራራ ጽላት ይወርድባታል፣ ሕግ ይሰጥባታል፣ ቃል ኪዳን ይጸናባታል፣ ሰውና ፈጣሪ ይነጋገሩባታል፣ የተባረከች ተራራ መለኮት ይገለጥባታል፣ ብርሃን ይሞላባታል፣ ምስጢር ይታይባታል፣ መምህሩ እና ደቀመዛሙርቱ ይሠባሠቡባታል፣ የተወደደች ተራራ ገዳም ይገደምባታል፣ ደብር ይደበርባታል፣ ያለ ማቋረጥ ጸሎት ይደረግባታል፣ ሱባዔ ይገባባታል።

የተመረጠች ተራራ የማያልፈው ንጉሥ በግርማው ይመላለስባታል፣ ለፍጥረት ሁሉ የሚያስደነግጠውን፣ በፍጥረታት አቅም የማይቻለውን ብርሃን ያሳይባታል፣ በተባረከች ተራራ የሞተውን አስነስቶ፣ በብሔረ ሔዋን የነበረውን ጠርቶ በአንድነት አሳይቷቸዋል። የብሉይ ዘመን ሰዎችን፣ ከሒዲስ ኪዳን ዘመን ሰዎች ጋር አገናኝቷቸዋል። የተወደደችውን ድምጽ አሰምቷቸዋል።

የተወደደች ተራራ ሰው ያማያያቸው፣ ቤት የሌላቸው ስውራን አበው ይኖሩባታል፣ ታሪክ ይከማችባታል፣ የተቀደሱ ንዋየ ቅድሳት በምስጢር ይኖሩባታል፣ ሥርዓት ይጸናባታል፣ ዕውቀት እንደ ዥረት ይፈስባታል፣ የጥበብ ነገር ይነገርባታል። የተወደደች ተራራ ነገሥታት ይሰፍሩባታል፣ ዙፋናቸውን ያጸኑባታል፣ በመኳንንቱ እና በመሳፍንቱ፣ በወይዛዝርቱ እና በጎበዛዝቱ፣ በጦር አበጋዞች እና በሊቃውንቱ ተከበው ይኖሩባታል፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ ለትውልድ የተገባውን፣ ለክብር የሚመጥነውን፣ ሕዝብ የማይበድለውን፣ ፈጣሪን የማያሳዝነውን ሥራ ይሠሩባታል።

እነኾ ይህች ተራራ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከከበሩት የከበረች፣ የጌታዋን ብርሃን እና ግርማ ለማየት የታደለች፣ ለምስጢር መግለጫ የተዘጋጀች፣ አስቀድሞ ገና በትንቢት እንደተነገረ በጌታዋ ደስ የተሰኘች ናት ደብረ ታቦር። ነብያት የተነበዩላት፣ አምላክ ግርማ መለኮቱን ይገልጥባት ዘንድ መረጣት፣ አዘጋጃት። ክርስቲያኖች ጌታቸውን ባሰቡ ቁጥር ያስቧታል፣ የእርሱን ዓበይት በዓላት ባከበሩ ቁጥር ያነሷታል፡፡ የአንድነቱን እና ሦስትነቱን ነገር በተናገሩ ጊዜ ይናገሩላታል በዓለ ደብረታቦር። የብርሃን በዓል፣ የመገለጥ በዓል፣ የምስጢር በዓል።

ይህች ሥፍራ በሀገረ እስራኤል ትገኛለች። በዚህች ሥፍራ የተፈጸመው ደግሞ ታላቅ በዓል ኾኖ ይከበራል። ወርሐ ነሐሴ አፍላጋት ባዘቶ መምስል ሲጀምሩ፣ አዝዕርት ሲያጌጡ፣ ምድር ከጎርፍ እና ከናዳ ስትረጋ ይህ በዓል ይከበራል። በዓለ ደብረታቦር። ኢትዮጵያውያን ቡሔ እያሉ ይጠሩታል። ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓት ይፈጸምበታል። ደብረ ታቦር፣ ትርጓሜው ተራራ ነው። በተራራ ላይ ያለ ተራራ፣ እንደ በሬ ሻኛ ከተራራ ላይ ያለ ተራራ ነው ይላሉ አበው። ይህን በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ተከታዮቿ በሥርዓቱ እና በሕጉ መሠረት ትውፊቱን ጠብቀው ያከብሩታል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደብረ ታቦር ኢየሱስ እና መካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር መጋቤ ምስጢር ኤፍሬም ቢራራ ስለ በዓለ ደብረታቦር ሲናገሩ ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን እና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ። ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ። ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መኾን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። እነሆም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው እና ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም ተብሎ እንደተጻፈ ይህች በዓል በዚያ ዘመን ጀምራ ትከበራለች ይላሉ።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ሥስት ጊዜ ሥስትነቱን እና አንድነቱን ገልጧል። የመጀመሪያው በቅድስት ድንግል ማርያም ሲጸነስ ፣ ሁለተኛው በማየ ዮርዳኖስ፣ በእደ ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ፣ ሦስተኛው ደግሞ በደብረታቦር ተራራ በተገለጠ ጊዜ ይላሉ መጋቤ ምስጢር። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም ያለ አምላክ ቃሉን ይፈጽም ዘንድ በደብረ ታቦር ተገለጠ። ቃሉን የማያጥፈው አምላክ ለሙሴ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ሙሴን ከሙታን አስነስቶ ቃሉን ፈጸመ። ተገለጠለትም። ኤልያስም ከብሔረ ሔዋን ተጠራ። በዚህ ቀን ትንሳኤ ሙታንን ያሳየበትም ነበር ነው የሚሉት መምህሩ።

ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የታቦቱ ምሳሌ ነው። ከሐዋርያት ሦስት እና ከነብያት ሁለት መገኘትም የአምስቱ ቀዳሲያን ምሳሌ ነው። ከሐዲስ ኪዳንም ከብሉይ ኪዳንም ሰዎች መገኘታቸው ቤተክርስቲያን በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ያለች፣ የነበረች መኾኗን ለማጠየቅ ነው ይላሉ የኔታ። ስለ ምን በደብረ ታቦር ተገለጠ የተባለ እንደኾነ አስቀድሞ ገና ትንቢት ተነገሯል። ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል ተብሎ። ይህ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በዚህ ሥፍራ ተገለጠ። የድል መንሻ ቦታም ስለኾነ ያንም ለማሳየት በደብረ ታቦር ተገለጠ። ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደፀሐይ አበራ። ልብሱም እንደበረዶ ነጭ ኾነ። ይህች ቀን ነብያትን እና ሐዋርያትን በአንድነት ፈጣሪያቸውን ያመሰገኑባት ናት። ምስጢረ መለኮት የተገለጠበት ነው የሚሉት።

በደብረ ታቦር ግርማ መለኮት በተገለጠ ጊዜ እረኞች በጎቻቸውን እና ከብቶቻቸውን አሠማርተው ይጠብቁ ነበር። ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ብርሃን ነበር እና የሰዓቱ መምሽት አይታወቅም ነበር። ይህን ያዩ እረኞች በብርሃኑ እየተደነቁ፣ የሰዓቱን መምሸት ሳያውቁ በዚያው ቆዩ። እነርሱ በብርሃን ውስጥ ናቸውና። ወላጆቻቸውም የልጆቻቸውን መምጣት በጠበቁ ጊዜ አልመጡም። በጨለመ ጊዜም ምን ነካቸው ብለው ፍለጋ ወጡ፡፡ ልጆቻቸውን ፍለጋ ሲወጡም ችቦ እያበሩ ነበር፡፡ ለልጆቻቸው ረሃብ ማስታገሻ ደግሞ ሙልሙል ይዘው ነበር፡፡

በዚያች ጊዜ የተፈጸው ሁሉ ዛሬም ድረስ ይፈጸማል፡፡ መምህሩ ሲናገሩ ባሕልና ሃይማኖት የሰው ልጅ መስታውቶች ናቸው፡፡ እረኞች ዛሬም ሃይማኖቱን ባሕል አድርገው የክርስቶስን መገለጥ ያስባሉ። በደብረ ታቦር የተፈጸመውን ይዘክራሉ። ሊቃውንትም እንደ ሥርዓቱ የመገለጡን በዓል በሃይማኖታዊ ሥርዓት ያከብራሉ ነው የሚሉት፡፡ በዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከወነው በመምህር እና በደቀመዝሙር ነበር። በዚህም ምክንያት ዛሬም የአብነት መምህራን ክርስቶስን ወክለው ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ነብያትን እና ሐዋርያትን ወክለው በዓሉን ያከብራሉ ይላሉ መጋቤ ምስጢር፡፡

ይህ በዓል በኢትዮጵያ በታላቅ ክብር ይከበራል፡፡ ስሙን ከስሙ በወሰደችው፣ በአምሳሉ በተሠራችው በደብረ ታቦር ደግሞ በዓለ ደብረታቦር ከፍ ብሎ ይከበራል፡፡ ስለ ምን ያሉ እንደኾነ ስሙን እና ክብሩን መጠበቅ የተገባ ነውና፡፡ መጋቤ ምስጢር ሲናገሩ የበጌምድሯ ደብረታቦር ከእስራኤሏ ደብረ ታቦር ጋር ትመሳሰላለች፡፡ ስሟንም ከእርሱ ወስዳለች፡፡ በደብረታቦር በዓለ ደብረታቦር ሲከበር ካህናት ነጭ ልብሰ ተክህኖ ይለብሳሉ፣ ሕጻናት የበግ ለምድም እየለበሱ፣ ጅራፍ እና ሙልሙል ይዘው ይመጣሉ። ሁሉም በተራራው ጫፍ በደብረታቦር በግርማ በሚኖረው በኢየሱስ ቤተክርስቲያን ይሠባሠባሉ፡፡

ያለ ምክንያት እና ያለ ምልክት የሚለበስ የሚፈጸም ሥርዓት የለም፡፡ ካህናቱ ነጭ የሚለብሱት ክርስቶስ ግርማ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ልብሱ በረዶ መስሎ ነበር እና ያን ለማጠየቅ ነው። ሕጻናት የበግ ለምድ መልበሳቸው፣ ጅራፍ እና ሙልሙል መያዛቸው በዚያ ጊዜ እረኞች ለብሰውት የነበሩትን ለማስታወስ ነው።

በሌላም የበግ ለምድ መልበሳቸው አማኞች በበግ መመሰላቸውን ለማሳየት ነው። እርሱም የበጎች እረኛ መኾኑን፣ እንደ በግ ታሥሮ መጎተቱን፣ እንደ በግ መሰዋዕቱን ለማሳየት ነው ይላሉ የኔታ። ልጆች ጅራፍ ስለ ምን ያዙ የተባለ እንደኾነ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ ተገልጧል፣ በጅራፍ ውስጥም ሦስት ነገር አለ። እንጨቱ፣ ማንገቢያው እና ጅራፉ። እነዚህ ሦስቱ ምስጢረ ሥላሴን ይገልጻሉ። ጅራፍም ሦስት አካላት እያሉት አንድ ጅራፍ ይባላል እንጂ ሦስት አይባልም። ቅድስት ሥላሴም አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አምላክ አይባሉም።

ከጅራፉ የሚወጣው ድምጽም ምሥጢረ መለኮቱን በገለጠበት ጊዜ የመብረቅ እና የነጎድጓድ ድምጽ ተሰምቷል። እግዚአብሔር አብ በደመና ኾኖ የምወደው ልጄ ይኼ ነው ብሎ ድምጹን አሰምቷል። የጅራፉ ድምጽም የአብ ድምጽ ምሳሌ ነው፣ የነጎድጓድ እና የመብረቁ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔር ወልድ ድምጹን አሠምቶ ማስተማሩንም ያመላክታል ነው የሚሉት። እረኞች በዓለ ደብረታቦር ጅራፍ እየተጋረፉ ይወድቃሉ። ይሄም ሐዋርያት ድምጹን ሰምተው የመውደቃቸው ምሳሌ ነው። ሙልሙሉ እና የሚበራው ችቦም በዚያ ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው ይዘውት የሄዱትን ለማሰብ ነው፡፡ ብርሃኑም መገለጡን ለማሰብ የሚደረግ ነው ይላሉ፡፡

በበዓለ ደብረ ታቦር እረኞች፣ ለእረኝነት ያልደረሱ ልጆች እና ሌሎች ጅራፍ እየፈተሉ፣ ለምድ ለብሰው “ ሆያ፣ ሆዬ….” እያሉ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡ በየመንደሮች እየሄዱ ያዜማሉ፡፡ በአበው እና በእመው እየተመረቁ ሙልሙል ይቀበላሉ፡፡ ምሥጋና እያቀረቡ ይዘዋወራሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለ በዓሉ ሲዜም ኖሯል፡፡
“ ደብረታቦር ከዋለ የለም ክረምት
ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እየተባለ፡፡

ከበዓለ ደብረታቦር በኋላ ከባድ ክረምት አለመኖሩን ሲናገሩ፡፡ ቡሔ የመገለጥ፣ የብርሃን እና የተስፋ በዓል ነውና በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ እነሆ ያቺ ቀን ደርሳለች እና በታላቅ ክብር እየተከበረች ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግብርና ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የ25 ዓመት ፍኖተ እቅድ ማብራሪያ እየተሰጠ ነው።
Next article“ከ39 ሺህ በላይ ማሳ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሲስተም ውስጥ በማስገባት የመሬት ግብይት ተፈጽሟል” የደቡብ ወሎ ዞን መሬት መምሪያ