
አዲስ አበባ: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ25 ዓመት የክልሉ የልማት ፍኖተ ካርታ ውስጥ ግብርናው በሚኖረው ድርሻ የማብራሪያ እና የግብዓት መድረክ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር የእቅዱ ገለፃ እና የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የዘርፉ መሪ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር) እንዳሉት በዚህ ባለ ሁለት ፍኖት የግብርና ዘርፍ ልማትን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን (ግብርና መር ኮሜርሻላይዜሽን) እና በገጠር ትራንስፎርሜሽን (የማኅበረሰብ አቀፍ አሳታፊ የተቀናጀ የገጠር ትራንስፎርሜሽን) አነስተኛ ባለ ይዞታዎች የግብርና ምርት ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ እቅድ መኾኑንም ዶክተር ሰኢድ አብራርተዋል።
የዚህ ዘርፍ ዓላማው ጥራት ያለው አኗኗር እና የሕይዎት ዘይቤ ማምጣት፣ የተሻለ ገቢ፣ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ማምጣት፣ ጠንካራ ተቋማት እና የነቃ ማኅበረሰብ፣ ፅዱ እና ዘላቂ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ላይ ያተኮሩ መኾኑም ተገልጿል፡
ተዋንያኑን በአግባቡ የለየ የተባለው ፍኖት የግብርና ስትራቴጂ እቅዱ ቴክኖሎጂ መር እና ኢኖቬሽን መር የመኾን አቅጣጫን መያዙም ተመላክቷል።
ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የግብርና ዘርፍ ራስን የመቻል እና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ግቦችን ለማሳካት ዓላማ ያለው መኾኑንም ዶክተር ሰኢድ አብራርተዋል። ግቦቹም ሁለት አቅጣጫዎች እንዳሉት ተጠቅሳል። በመጀመሪያው 10 ዓመት የአዝርእት ዘርፍ እቅድ በ5 ዓመቱ በ8 ነጥብ 8 ተጨማሪ እሴትን ማሳደግ፤ በሁለተኛው 5 ዓመት ደግሞ 6 ነጥብ 9 በመቶ እንዲያድግ መታቀዱም ተገልጿል። የእንስሳት ዘርፍም ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ እንዲኾን ትልም መያዙም ተገልጿል።
ዘርፉ በሥጋትነት ከያዛቸው ነጥቦች መካከል ግብርና እንደ አዋጭ ኢንቨስትመንት ባለመታየቱና ዝቅተኛ መዋለ ንዋይ ፈሰስ እሚደረግ መኾኑ ለእድገት እና ልማት ያለ ዝቅተኛ አመለካከት ለእቅዱ ስኬታማነት እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!