
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተቋማት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እና መጀመሪያ ላይ ግዥን ያለ እቅድ ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በነዚያ ወቅቶች ግዥ እና ክፍያዎች ይበዛሉ፡፡ ይሁንና ግዥ በእቅድ፣ በአሳታፊነት እና በተጠያቂነት መርህ ካልተከናወነ ጉዳት እንዳለው ይታወቃል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ገንዘብ መምሪያ የግዥ እና ንብረት ቡድን መሪ ማየት ደመቀ በግዥ ወቅት ”መንግሥትን አምነው፣ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ግብር ሊከፍሉ የተዘጋጁ ሰዎች መሳተፍ አለባቸው” ይላሉ፡፡ ከግልጽ ጨረታ ውጪ ያሉት አማራጮች የሚፈጸሙበት ምክንያት ቢኖርም ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መኾናቸውን ነው አቶ ማየት የገለጹት፡፡
በመርህ ደረጃ ግዥ በአንደኛው እና በሁለተኛው ሩብ ዓመት እንዲፈጸም ቢመከርም የተለመደው ግን ከዚያ በላይ ነው ያሉት አቶ ማየት በእቅድ ያልተመራ ግዥ ገንዘብ ቆጣቢ፣ ውጤታማ እና ቀልጣፋ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመት መጨረሻ የሚፈጸም ግዥም በእቅድ አለመመራትን ያመለክታል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የመንግሥት ግዥ፣ ንብረት አሥተዳደር እና ኦዲት ክትትል ዳይሬክተር ቻላቸው ካሂል ግዥ የሚፈጸመው በበጀት ዓመቱ የሚፈለጉ ዕቃዎችን ለማቅረብ እና ውስን በጀትን በአግባቡ ለመጠቀም ነው ብለዋል፡፡
ግዥ መፈፀም ያለበት በበጀት ዓመቱ ለሚከናወኑ ፊዚካል ሥራዎች ማስፈጸሚያ ግብዓቶች እንጂ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ወይም በጀት እንዳይተርፍ ለመጨረስ አለመኾኑን ተናግረዋል፡፡ ግዥን በእቅድ አለመፈጸም ሃብትን ያባክናል፤ ለሙስናም ያጋልጣል ሲሉም አክለዋል፡፡
ያልታቀደ ግዥ መንስኤዎች ግዥን በትኩረት አለማቀድ እና በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ከረጂ ድርጅቶች የሚገኝ በጀት እንደኾኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በጀቱ ”ከሚቃጠል” እንግዛበት በሚል የሚፈጸም ግዥ መኖሩን ነው አቶ ቻላቸው የጠቀሱት፡፡
ገንዘብ ቢሮ ችግሩን ለመከላከልም ድጋፍ እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ቻላቸው ኀላፊዎች ተግባሮችን ሲገመግሙ በጀትንም መገምገም እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
በጀት የሚፈቀደው ፊዚካል እቅዱን ለመተግበር እንደኾነ አቶ ቻላቸው ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት የተፈቀደ በጀት በሥራ ላይ ካልዋለ በተከታዩ በጀት ዓመት ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን በጀትን ተጠቅሟል ለመባል አላስፈላጊ ግዥ ይከናወን ማለት እንዳልኾነም አስታውሰዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቻችን ያልታቀደ ግዥን በመፈጸም የሀገርን ሀብት ማባከንን ለመከላከል ቀድሞ ከማስተማር፣ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ እና የኦዲት ግኝቶችን ሪፖርት ይደረጋል ከማለት ያለፈ የተጠየቀ ተቋም፣ ባለሙያ እና ኀላፊ አልጠቀሱም፡፡
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደሳለኝ ነጋ መሥሪያ ቤታቸው በሚያደርገው ኦዲት ያልታቀደ ግዥን መፈጸም አለመፈጸሙንም እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡ ተወዳዳሪዎችን (አቅራቢዎችን) ግምት ውስጥ ስለማያስገባ ጉዳቱ ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ በኦዲትም የገንዘቡ ማነስ እና መብዛት ሳይኾን ግዥው የተፈጸመበት ኹኔታ ግምት ውስጥ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ያልታቀደ ግዥ ከሚፈጸምባቸው ግዥዎች መካከል አንዱ የአገልግሎት ግዥ ነው፡፡ በየተቋሙ ለወጣው ወጪ ተመጣጣኝ ግልጋሎት መገኘቱ ግምት ውስጥ ሲገባ አይስተዋልም፡፡ ለዚህም ማሳያው ግንባታዎች ሳይጠናቀቁ እና ርክክብ ሳይደረግባቸው መፍረስ ይጀምራሉ፡፡
የክዋኔ ኦዲትን ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ማየት መጀመሩን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡ በምሳሌነትም በሊዝ ላይ ያለን ችግር በኦዲት እያገኘን ነው፤ የተፈጸመው ግዥ ለወጣበት ወጪ ተመጣጣኝ አገልግሎት እየሰጠ ነው ወይ ተብሎ ይመረመራል ብለዋል፡፡
ተቋማት ያልፈጸሙትን ተግባር አሳውቀው በሚቀጥለው በጀት ዓመት በጀት ማስመደብ እንጂ በጀቱን ለመጨረስ ያልተገባ ግዥ መፈጸም እንደሌለባቸው የገለጹት አቶ ደሳለኝ በዚህ መርህ ከመገዛት ይልቅ ያልታቀደ ግዥ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ በመኾኑም የሚገዙት ዕቃዎች የጥራት ችግር ያለባቸው ሲኾኑ ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡
የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያልታቀደ ግዥን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ኀላፊነቱ ኦዲት አድርጎ ሪፖርቱን ለክልሉ ምክር ቤት እስከ ማቅረብ ድረስ መኾኑን ነው አቶ ደሳለኝ የገለጹት፡፡ የኦዲት ግኝቶች መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ የየደረጃው ምክር ቤቶች ኀላፊነት መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የተገኙ ግኝቶች ከሚመለከተው አካል ጋር በመተባበር መፍትሄ እንዲያገኙ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ቢሠራም ብቻውን በቂ ባለመኾኑ ምክር ቤቶች ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ግዥ ፈጻሚ አካል በፈጸመው ጥፋት ተጠያቂ የሚኾንበት አሠራር መተግበር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
ያልታቀደ ነገር ጥፋት አለው ያሉት ዳይሬክተሩ በክልል ደረጃም የሚመለከታቸው ተቋማት መከታተል፣ መገምገም እና ጥፋቱን መከላከል ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት ብክነትን ተከታትሎ የሚያስመልስ እና እልባት የሚያሰጥ ”የመንግሥት ወጪ ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ” በቅርቡ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ኮሚቴ ያልታቀደ ግዥን እና አባካኝ የበጀት አጠቃቀምን እንደሚከታተል ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!