
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ የፖለቲካ እና የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው። በበጀት ዓመቱ የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች ቢገጥሙም በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ጥረት መደረጉን የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በአንድ በኩል የጸጥታ ችግሮችን መፍታት በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ በችግር ምክንያት የተስተጓጎለውን ለማካካስ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል። በተለይ የኑሮ ውድነትን የሚፈቱ እና የሕዝቡን ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በ2017 በጀት ዓመት ትኩረት ይሰጣቸዋል ነው ያሉት።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ያለፈው በጀት ዓመት በቀውስ ጊዜ የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲሁም የልማት ሥራዎች የተሳለጡበት ነው ብለዋል።
የከተማ ግብርና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መከላከል፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ሌሎችም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት መኾናቸውን አብራርተዋል። በፖለቲካ ሥራዎችም የተሻለ አፈጻጸም እንደነበር ተናግረዋል። ለዚህም የቀውስ ጊዜ መሪዎች ሚና ላቅ ያለ እንደነበር አንስተዋል።
የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በአማራ ክልል ላጋጠመው የሰላም እጦት እንደ አንድ መነሻ ምክንያት መኾኑን ያመላከቱት ዶክተር አሕመዲን በችግሩ ምክንያት የገጠመውን ጉዳት ለመቀልበስ የአምስት ዓመት የቁጭት ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በተሻለ ተነሳሽነት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር አሕመዲን ዕቅዱ እንዲሳካም መሪዎች የላቀ ኀላፊነት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የከተማ፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በዚህ መድረክ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅም ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!