“በቡሄ በዓል ጅራፍ የማጮህ ልምድ ምሳሌው መለኮታዊ ድምጹን ለማመላከት ነው” መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ

40

ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ኀይሉን የገለጠበት የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በደብረ ብርሃን ከተማ የደብረ ገነት ቅዱስ ኡራኤል እና አንቀጸ ምህረት የቅዱስ ሚካኤል አድባራት አሥተዳዳሪ መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ በዓሉ ለቤተክርስቲያኗ አማኞች ልዩ ትርጉም ስላለው በልዩ ሁኔታ ደምቆ ይከበራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ኀይሉን የገለጠበት የደብረ ታቦር በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 በዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በልዩ ልዩ ሁነቶች ነው የሚከበረው። መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ በታቦር ተራራ በርካታ ገቢረ ተዐምር መፈጸሙን ይናገራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ የምስጢር ሐዋርያት የሚባሉትን ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዩሀንስን እና ቅዱስ ያዕቆብን በታቦር ተራራ ይዞ በመውጣት በነሐሴ 13 ቀን መለኮታዊ ክብሩን በመግለጽ ፍጹም አምላክ መኾኑን ያሳየበት ነው ይላሉ።

ቡሄ የሚለው የደብረ ታቦር በዓል ሌላኛው መጠሪያ ከተፈጥሮ ጋር የሚገናኝ ነው ብለዋል መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ።
ቡሄ ደማቅ፣ በራ፣ የተገለጠ የሚል ትርጓሜ ሲይዝ በዓሉ የሚከበረው የክረምቱ የጨለማ ወራት አልፎ ሰማዩ ከጭጋጋማነት ወደ ብርሃንነት የሚለወጥበት የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ወቅት መኾኑን ተከትሎ የተሰጠው ስያሜ እንደኾነ መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ ያስረዳሉ።

የምወደው የምወልደው ልጄ ነው የሚላችሁን ስሙት የሚል መለኮታዊ ድምጽ በደመና በመሰማቱ ያን መሠረት ተደርጎ ጅራፍ እንደሚጮህ አስረድተዋል፡፡ ጅራፍ የማጮህ ልምድ ምሳሌውም መለኮታዊ ድምጹን ለማመላከት መኾኑንም ጠቁመዋል።

ከበዓለ ደብረ ታቦር ጀምሮ የደመና መገለጥ ክረምቱ እየቀለለ መምጣቱን አመላካች ነው የሚሉት መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ ለዚህም ቡሄ እና ንጋት የሚመሳስሉበትን የአበው ብሂልን አንስተዋል።

“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” የሚለው ብሂል ተስፋን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ የሰው ልጅ ጉዞና ተስፋ በደብረ ታቦር በዓል ይታያል ሲሉ የበዓሉን ታላቅነት ገልጸውታል መላዕከ ገነት ቀሲስ ኃይሌ አየለ። የደብረ ታቦር በዓል ከቤተክርስቲያኗ እስከ አማኙ ድረስ ሃይማኖታዊ እና ተውፊታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበርም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ2017 የበጀት ዓመት የፀጥታ እና የልማት ሥራዎችን አስተሳስሮ በመፈፀም ዞኑን ወደ ተሟላ ሰላም ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተመላከተ።
Next article“የጸና እና ቁርጠኛ መሪ በችግር ውስጥም ኾኖ ለውጥ ማምጣት ይችላል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው