
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎጃም የዞን፣ ወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኀላፊዎች የተሳተፋበት የ2017 የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ዕቅድ ውይይት ተካሂዷል። የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለሕዝቡ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት በኩል የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ማረም እንደሚገባ የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ ጠቁመዋል። ችግሩ ለሕገ ወጥነት፣ ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት እንዲስፋፋ ማድረጉንም ኀላፊው ገልፀዋል።
በየጊዜው የተጠራቀሙ ችግሮች አሁን ላይ እንደ ክልል እና ዞን ላጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ ችግር አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሉት ኀላፊው በተያዘው በጀት ዓመት ተቋማዊ ኀላፊነትን የመወጣት አቅምን በማሳደግ ሕዝቡን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይጠይቃል ብለዋል።
በዞኑ ሰላም እና ልማትን አስተሳስሮ ለመሥራት የአመራሩን ትኩረት የሚጠይቅ በመኾኑ ውይይት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። እንደ ዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰፊ የልማት አቅሞች ያሉበት ነው ያሉት አቶ ዓባይ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ በዞኑ የተሟላ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!