“የዘመን ኮከቦች፣ ታላቅ ሀገር አውራሾች”

53

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ሰዎች አሉ ዘመንን የሚያሳምሩ፣ የማይቻል የሚመስልን ታሪክ የሚሠሩ፣ በታሪክ የከበሩ፣ በጠላቶቻቸው የተፈሩ፣ ከመቃብር በላይ የሚኖሩ፣ መሞታቸው የሚረሳ፣ ክብራቸው በሠርክ የሚወሳ።

እነዚህ ጥንዶች በታሪክ ከከበሩት፣ ከመቃብር በላይ ከዋሉት፣ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን በሚገባ ከተረዱት፣ ለክፉ ዘመን ድልድይ ሠርተው ካሻገሩት፣ ለታላቁ ሀገር ታላቅ ታሪክ ከሠሩት፣ በዘመናት እንደ ንጋት ኮከብ ከሚያበሩ ታላላቆች መካከል ናቸው። እነርሱ የዘመን ከዋክብት ናቸው ለትውልድ አብርተዋል፣ በጨለመ ጊዜ መውጫ መንገድ አሳይተዋል፣ በብልሃት ሀገር መርተዋል፣ በጀግንነት ተከብረዋል፣ በግርማቸው ተፈርተዋል፣ በጥበባቸው አስቸጋሪ ጊዜያትን አልፈዋል። ኢትዮጵያን አስከብረዋል፣ ኢትዮጵያዊነትን አጽንተዋል፣ አንድነትን ከፍ ከፍ አድርገዋል።

በተዋበ እልፍኝ ውስጥ ትዳራቸውን፣ ባማረ ዙፋን ላይ ኾነው ሀገራቸውን መርተዋል። እቴጌ፣ እምዬ እየተባባሉ ይጠራራሉ፣ እልፍኝ ዘግተው ስለ ሀገራቸው መልካም ነገር ይመክራሉ፣ መኳንንቱን እና መሳፍንቱን ጠርተው ለሀገር የሚበጀውን፣ ጀግና የሚያደረጀውን፣ ሕዝብ የሚጠቅመውን፣ ዳር ድንበር የሚያስከብረውን፣ ነጻነት የሚያጸናውን፣ በክብር እና በፍቅር የሚያኖረውን ምክር ያዋጣሉ። በችሎት ፍርድ እንዳይጓደል፣ ደሃ እንዳይበደል ያደርጋሉ።

ንጉሡ እንደ እናት አዛኝ ናቸውና እምዬ እየተባሉ ይጠራሉ። ንግሥቷ ብልህ ናቸውና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ይባላሉ። ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ።

ፈጣሪ ከዘመናቸው ያለፈ ለትውልድ የሚበቃ ታሪክ በጋራ ሥሩ ሲላቸው እቴጌን ከበጌምድር፣ እምዬን ከሸዋ አገናኛቸው። ጥንዶቹ በጋራ እየመከሩ የግዛት አንድነትን አጠናከሩ፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ይከበር ዘንድ ያለ እረፍት ሠሩ። የኢትዮጵያን ነጻነትም በጀግንነት አጸኑ።

በዓድዋ ሰማይ ሥር ቅኝ ገዥን ድል አድርገው በሌላ ጥቁር ሀገር ያልተሞከረን ገድል አሳዩ፣ በዚህ ገድላቸው የሮምን ሹማምንት፣ የቅኝ ገዥዎችን ነገሥታት አስደንግጠዋል፣ በሀገራቸው በኢትዮጵያ ያልነበሩ ሥልጣኔዎችን አምጥተዋል፣ አንድነት የትውልድ ውርስ ይኾን ዘንድ ሠርተዋል። የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ነጻነት እንዳይነካ አድርገዋል። ትውልድ ሁሉ ለሀገር ነጻነት እንዲኖር የአደራ ቃል አስቀምጠዋል። እነርሱ የዘመን ኮኮቦች፣ ታላቅ ሀገር አውራሾች ናቸው።

አበው ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ ይላሉ። እቴጌና እምዬ ግን ከአንድ ወንዝ ብቻ አይደለም የተቀዱት። ውልደታቸውም በአንድ ቀን ኾነ እንጂ። ምንም እንኳን የዓመታት ልዩነት በመካከላቸው ቢኖርም እቴጌ እና እምዬ የተወለዱት በተመሳሳይ ቀን ነበር። ምን አልባት ፈጣሪ በታሪክ ለየት አድርጎ ሲያስቀምጣቸው ይኾናል እንዲህ አድርጎ ወደ ምድር የላካቸው።

ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው “እቴጌ ጣይቱ በነሐሴ 12 ቀን በ1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ በደብረታቦር ከተማ ተወለዱ። ተጠምቀው ክርስትና የተነሡት በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው። እቴጌ ዳዊት የደገሙ፣ በየአድባራቱ እየተዘዋወሩ ትምህርት የተማሩ ናቸው። የግዕዝ ቋንቋ አጣርተው ያውቁ ነበር። እቴጌ በማሕደረ ማርያም ኾነው ይማሩ፣ መጻሕፍትን ይቀጽሉ በነበሩበት ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን መጋረጃ ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ ነበሩ” ብለው ከትበዋል።

የትዳር አጋራቸው ምኒልክ ደግሞ እርሳቸው በተወለዱ በአራት ዓመታቸው፣ በልደታቸው ቀን ተወለዱ። ምኒልክ የኃላ ባለቤታቸው እና ግርማቸ፣ ዘውዳቸው እና ካባቸው የኾኑት እቴጌ ጣይቱ በተወለዱበት ቀን በነሐሴ 12 ተወለዱ።

ጳውሎስ ኞኞ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው” ምኒልክ በ1836 ዓ.ም ነሐሴ 12 ቀን ቅዳሜ ዕለት ተወለዱ። አባታቸው ኃይለ መለኮት ሣሕለ ሥላሴ ሲኾኑ እናታቸውም ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ ይባላሉ” ብለው ጽፈዋል።

ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው” ምኒልክ በነሐሴ 12 ቀን በ1836 ዓ.ም አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ተወልደው፣ ካባታቸው ከንጉሥ ኃይለ መለኮት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር በአንጎለላ፣ በአንኮበር እና በደብረ ብርሃን እየተዘዋወሩ ቆይተው በኋላም የሕጻንነትን እና የወጣትነት ጊዜያቸውን በጎንደር እና በደብረታቦር ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር እንደ ልጅም፣ እንደ አማችም ኾነው አሳልፈዋል” ብለው ከትበዋል።

የሕይወት አጋጣሚ ምኒልክ ከሸዋ ወደ ጎንደር አምጥቷቸው በቴዎድሮስ እልፍኝ ኖሩ። በዚህም ጊዜ ስለ እቴጌ ጣይቱ ይሰሙ ነበር ይባላል። ዓመታት አልፈው ምኒልክ ከቴዎድሮስ እልፍኝ ወጥተው ወደ ተወለዱበት ሀገር ሸዋ ሄዱ። ሸዋ በሄዱም ጊዜ በአባታቸው ወንበር ላይ ተቀመጡ። የሀገሬው ሰውም ተቀበላቸው። ገዥዎቹም ገበሩላቸው።

ንጉሥ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ከኾኑ በኋላ አስቀድሞ ገና በጌምድር ከቴዎድሮስ ጋር ሳሉ ይሰሙት የነበረውን የጣይቱን ብልሕነት የበለጠ የሚያውቁበት ዕድል አገኙ። ይህም የኾነው የጣይቱ ወንድሞች ፊታውራሪ አሉላ ብጡል እና ራስ ወሌ ብጡል ከአጼ ቴዎድሮስ ከድተው ሸዋ ወደ ምኒልክ በመሄዳቸው ነው ይላሉ ቀኝ አዝማች ታደሰ። በወንድሞቻቸው ምክንያት የእቴጌን ብልሕነት የበለጠ አወቁ። ከዚያም ባለቤታቸው ይኾኑ ዘንድ ወደዱ። ምኒልክም በወጉ መሠረት ከጣይቱ እናት እመት የውብዳር ዘንድ ፈቃድ አስጠየቁ። ፈቃድም አገኙ።

በ1871 ዓ.ም ጣይቱን ለማስመጣት በቤተ መንግሥት በተደረገው ምክር መሠረት አለቃ ተክለማርያም ወልደ ሚካኤል ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ተላኩ። በዚያም አስፈላጊው ሁሉ በተፋጠነ ሁኔታ ተሟልቶ ጣይቱ ወደ ሸዋ ተወሰዱ። ሸዋም በደረሱ ጊዜ ምኒልክ ታላቅ አቀባበል አደረጉላቸው። ከዚያም እቴጌ ጣይቱ ከወንድማቸው ከራስ ወሌ ቤት ቆዩ። ጋብቻቸውም ሚያዚያ 25/1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተፈጸመ ብለዋል ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ።

በነሐሴ 12 በበጌምድር ደብረታቦር እና በሸዋ አንጎለላ የተገኙት ታላላቆቹ ሰዎች በአንድ ካባ ሥር ተቀምጠው ለቁርባን በቁ። እስከሞት የጸና ቃል ኪዳንም አሠሩ። ቃልሽ ቃሌ ነው፣ ቃልህም ቃሌ ነው ተባባሉ። ምኒልክ ከሸዋ ንጉሥነት ወደ ንጉሠ ነገሥትነት በተሸጋገሩ ጊዜም ጣይቱም እቴጌ ተብለው ተቀቡ።

ተክለጻድቅ ስለ ንግሥናቸው ሲጽፉ ” ታላቅ ዳስ እንጦጦ ላይ ተሠርቶ ድግሡ በየአይነቱ ተደግሶ በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ባሉበት በጥቅምት 25 ቀን በ1882 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው በታላቅ ሥነ ሥርዓት ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው 25 ዓመት ሙሉ የጠበቁትን የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ጫኑ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ጣይቱ ብጡልም እንደ ደንቡ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓተ ንግሥ በተደረገ በሦስተኛው ቀን በጥቅምት 27 ቀን የእቴጌነት ዘውድ ጫኑ” ብለዋል።

እኒህ ንጉሥ እና ንግሥት በዘውዳቸው ዘመናት ለኢትዮጵያ ታላቅ ነገርን አደረጉ። “ሰው ሁሉ በተፈጥሮው እኩልነት ያለው ሲኾን በታሪኩ ይለያያል። አንዱ ከአንዱ በልጦ ይገኛል። አንዱ ለቆመለት ከፍተኛ ዓላማ የግል ጥቅሙን መሥዋዕት ለማድረግ የሚያበቃው ጀግንነት ሲኖረው ሌላው ተቃራኒውን ፈለግ በመከተል ኑሮውን ይመራል። የጀግና ልቦና ለሀገሬ እንጂ ለራሴ ከሚል ግላዊ ሀሳብ የራቀ ነው” እንዳሉ ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ እኒህ ጥንዶች ልቦናቸው ለሀገሬ የሚል ነበር።

ለሀገራቸው በማለታቸውም በዘመናቸው የነበረው ብቻ ሳይኾን ከዘመናቸው በኋላ የተከተላቸው ትውልድ የሚኮራበት ታሪክ ሠርተዋል። በአንድነት እየመከሩ፣ በአንድነት እየመሩ ታላቅ ሀገር አቆይተዋል። እኒህ ጥንዶች የኢትዮጵያ ታሪክ እና ክብር ሳይነካ ተጨማሪ ሥልጣኔ እና ክብር የጨመሩ ናቸው። ዘመናዊ ትምህርት እንዲኖር፣ የባቡር ትራንስፖርት እንዲጀመር፣ ማተሚያ ቤት፣ ስልክ፣ ሆቴል፣ የቧንቧ ውኃ፣ ዘመናዊ ሆስፒታል እንዲኖር እና ሌሎች አያሌ ሥልጣኔዎች እና አዳዲስ ነገሮች እንዲጀመሩ አድርገዋል።

እቴጌ እና እምዬ በመደጋገፍ ሀገራቸውን የመሩ ብልህና ጥበበኞች ነበሩ። “ምኒልክ ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን በመንግሥቱ የፖለቲካ እና የአሥተዳደር ሥራ ሲያስገቡ ከመደገፍ እና ከማበረታታት በቀር ሴት ነሽ አንቺ ምን አገባሽ የሚለው ስሜት አልነበረባቸውም። ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ የሚል ማሕተም አሠርተው በበኩላቸው የአሥተዳደር የቅርብ ረዳት ሲኾኑ የኢትዮጵያ ብርሃን እኔ ነኝ እንጂ አንቺ አይደለሽም የሚል የዝና ሽሚያ በመንፈሳቸው አላሳደሩም” ብለው ጽፈዋል ተክለጻድቅ።

ተክለጻድቅ ፈረንሳዊውን ሙሴ ሔግ ለሩን ጠቅሰው ጽሑፋቸውን ሲቀጥሉ ፈረንሳዊው ሰው “የኢትዮጵያ አውራጃዎችን ጎብኝቶ በምኒልክ ፊት የደረስሁባቸውን የወረዳዎች የወንዞች እና የተራራዎች ካርታ በፊታቸው ዘርግቼ አብረን ስንመለከት የጋራዲቢን ትልቁን ተራራ የምኒልክ ተራራ ብዬ ልሰይመው ነው ብዬ ባመለክታቸው የለም አይኾንም በግዛቴ በኔ የተሰየመ ሌላ ተራራ አለና ይኸኛውን ስያሜ ለግርማዊት እቴጌ ጣይቱ አድርገው የሚል መልስ ሰጡኝ ” ብሏል በማለት ጽፈዋል። እምዬ እስኪ በል ምን እናድርግ፣ እቴጌ እስኪ በይ ምን እንሥራ እያሉ ሃሳብ እያዋጡ ፣ ሀሳባቸውን በአንድነት እየገመዱ ለሀገር ሢሠሩ ኖሩ።

ይህን የመሰለው መተሳሰብ፣ ከቅናት እና ከምቀኝነት የራቀ ሀሳበ ሰፊነት የኢትዮጵያን ሕዝብ መኳንንት እና መሳፍንት በአንድ የሥልጣን ዘንግ አቁሞ የአውሮፓ ኀያል መንግሥትን ድል እንዲመታ አድርጓል። ዘመናቸው ስኬታማ እንዲኾን ያደረገው፣ በቤተ ዕምነቱ እና በቤተ መንግሥቱ እንዲወደዱ ያደረጋቸው ብልሃታቸው፣ የአንድነት ሃሳባቸው እና ሀገር ወዳድነታቸው ነው ይባላል። እኒህ ታላላቅ ሰዎች ታላቅ ነገር አድርገዋልና በትውልድ ይዘከራሉ። እንኳንም ተወለዳችሁ!!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”