
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ምልከታ አድርገዋል::
ዶክተር አሕመዲን “በከተማ አሥተዳደሩ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል” ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊ ተግባር በመኾኑ ከክረምቱ ባሻገር በሌሎችም ጊዜያት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማ አሥተዳደሩ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 400 ቤቶችን በአዲስ እና በጥገና ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ የ159 የአዲስ ቤቶች ግንባታ እና 130 ቤቶች ጥገራ ሥራን ማስጀመር እና መሥራት ተችሏልም ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ቤቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለአቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን እና ሴቶች ከማስረከብ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ያነሱት ከንቲባው ችግሮቹን በመለየት እና በመገምገም በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ክትትል እያደረጉ ስለመኾናቸውም ነው የገለጹት፡፡
የተጀመሩ ቤቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ከግብዓት አቅርቦት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችን እስከ ቀበሌ ድረስ በማጣራት ፈጣን ማስተካከያ እና ምላሽ እንዲያገኙ ይሠራል ያሉት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ ናቸው::
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!