“የአማራ ክልል የ25 ዓመታት ዕቅድ ለመሪዎች ብቻ ሳይኾን ለሁሉም የክልሉ ሕዝብ እንደየደረጃው ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውይይት ይደረግበታል” አቶ ተመስገን ጥሩነህ

75

አዲስ አበባ: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ25 ዓመታት (2018 እስከ 2042 ዓ.ም) “የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ” እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በፌዴራል ደረጃ ካሉ የአማራ ተወላጅ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ምክክር እየተደረገ ነው።

ዕቅዱ በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ክልሉ ያለውን ሁለንተናዊ አቅም በመጠቀም ሁሉን አቀፍ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል እንደኾነም ተነግሯል።

ይህን የአንድ ትውልድ የማክሮ ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ለመተግበር ለባለፉት ስድስት ወራት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውም ተገልጿል።

በመኾኑም ዕቅዱ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ሰፊ ውይይት ተደርጎበት እና ማሻሻያዎች ተጨምረውበት ወደ ሥራ እንዲገባ ዛሬ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውይይት ከክልሉ ተወላጆች የፌዴራል የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

በዚህ “የአማራ ክልል አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ” የምክክር መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የአማራ ተወላጅ የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ”አሁን ያለውን የክልሉን ሁኔታ ያገናዘበ እና ከችግሮች መልካም ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የጸጥታ ችግር አጋጥሞታል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ አመራር መደበኛ ሥራውን ከማከናወን በተጨማሪ የክልሉን ጸጥታ በማስከበር ላይ በመኾኑ ለትግበራው የመሪዎች ቁርጠኝነት ይጠይቃል ነው ያሉት።

ይህን የአንድ ትውልድ ዕቅድ ለማቀድ እና ክልሉ የገጠመውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩን መነሻ ምክንያቶች እና የመንግሥት ችግር እና ሚና ምንድን ነው የሚለው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል።

የክልሉን ሁሉን አቀፍ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ደግሞ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የረጂም ጊዜ ዘላቂ ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱንም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

ይህን የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ ለማቀድ ለባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ባለሙያዎችን ያሳተፉ ትግበራዎች መሠራታቸውም ተገልጿል።

በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ደግሞ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅት እና የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ጊዜ በመኾኑ ሁሉንም የክልሉ ማኅበረሰብ እና ዲያስፖራውን ያካተተ ውይይት ሲደረግበት ይቆያል ነው ያሉት።

በመኾኑም በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ደረጃ በኀላፊነት ያሉ የክልሉ ተወላጆች ያላቸውን ግብዓት በማካተት ለክልሉ ዕድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ርእስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቅርበዋል።

የሥራ ኀላፊዎቹ ሰነዱ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ ግብዓት በመጨመር እና ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ይህ የውይይት መድረክ የክልሉ ሕዝብ ካለበት ግጭት እና መከራ የሚወጣበት የታሪክ እጥፋት መኾን አለበት ብለዋል።

የ25 ዓመት የአማራ ክልል ዕቅድ ሲታቀድ በሀገሪቱ ያሉ እና የሌሎች ክልሎች ልምድ እንዲሁም ቀውስ ውስጥ የነበሩ እና ከቀውስ የወጡ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች ተወስደዋል ነው ያሉት።

ዕቅዱ ለመሪዎች ብቻ ሳይኾን ለሁሉም የክልሉ ሕዝብ እንደየደረጃው ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውይይት የሚደረግበት ይኾናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪዎች በፌዴራል ደረጃ ኀላፊነት ቢኖርባቸውም በክልሉ ውስጥ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እንደ ክልል ተወላጅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

በምክክር መድረኩ “የአማራ ክልል የዕድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ ለመተግበር እና ከ25 ዓመት በኋላ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ መልካም ዕድሎች፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እና የመፍትሔ ሃሳቦች እንዲሁም ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ዝርዝር ጉዳይ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያው ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር) ቀርቧል።

በተጨማሪም የክልሉ መልካም ዕድሎች፣ የስኬት መንገዶች እና እያንዳንዱ ዘርፍ ከዚህ በፊት የነበረበት፣ አሁን ያለበት እንዲሁም በቀጣይ አምስት ዓመት እና 25 ዓመት መድረስ የሚችልበት መዳረሻ ነጥቦች በዝርዝር ቀርበዋል።

ዘጋቢ፡- አደራው ምንውዬለት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳምንቱ በታሪክ
Next article“በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)