
👉“የአማርኛ ሰዋሰው አባት”
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም ሸዋ ጅሩ ውስጥ እምቧጮ መግደላዊት በተባለ ሥፍራ ነው የተወለዱት። አራት ዓመት ሲኾናቸውም ፊደል መቁጠር ጀመሩ። የትምህርት አቀባበላቸው ጥሩ ስለነበር የዜማ ትምህርት ጀምረው የድጓ ትምህርታቸውን በግሩም ሁኔታ አጠናቀቁ፡፡
በ1901 ዓ. ም ለተጨማሪም የቅኔ ትምህርት ወደ ጅሩ በመሄድም ቅኔን ተምረው በ1902 ዓ.ም በመቀኘት በ1904 ዓ. ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ቅኔን መዝረፍ ተያያዙት፡፡
“አሁን ሥራ የምይዝበት ሰዓት ነው” በማለት ሥራ አፈላልገው በ1906 ዓ. ም የጸሐፊነት ሥራ ያዙ። አንድ ዓመት ከአራት ወርም በጸሐፊነት አገለገሉ፡፡ በዚህም መርካት ባለመቻላቸው በ1907 ዓ.ም ነሐሴ ወር የሻለ ትምህርት ሽተው ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ በቀሰሙት ትምህርትም የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ መሥራት ጀመሩ፡፡
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ በ1910 ዓ. ም ወደ ሐረር አቅንተውም ሐዲሳቱን በመከለስ ትምህርታቸውን በመቀጠል በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በ1912 ዓ.ም በመንግሥት ተቀጥረውም እንደገና የትርጓሜን ረቂቅ ማውጣት እና በባለሙያው ሊቅ አረጋግጠው ንባቡን ከነትርጉሙ ለህትመት የማዘጋጀት የጽሕፈት ሥራ ጀመሩ። በዚህ ዓይነት ሥራ እያሉ የውጭ ሀገር ቋንቋን ለመማር ስለተመኙ በ1913 ዓ.ም ከዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት ገብተው እንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሩ። በዚህ ወቅትም “ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው” መጻሐፍን አዘጋጁ፡፡
የጽሕፈት ሥራቸውን አጠናክረው በመቀጠላቸውም “ብርሃንና ሰላም” ተብሎ በተሰየመ ጋዜጣ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም መርስዔ ኀዘን ጋዜጠኛ ኾነው ተዛውረው በዋና ጸሐፊነት ይሠሩ ጀመር። በሥራቸው በሳልነት በንጉሱ ሳይቀር ተወደሱ፡፡ በመኾኑም በሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ተከፈተ፡፡ በወቅቱ የግዕዝ እና የአማርኛ ቋንቋዎችን ሊያስተምር የሚችል ሊቅ ተፈለገ፡፡ በንጉሱ አቅራቢነትም መምህር ኾነው ተመደቡ፡፡
ከመምህርነቱ ጎን ለጎንም የድርሰት ሥራቸውን እያከናዎኑ ነበርና “ትምሕርተ ሕፃናት” የተባለ መጽሐፍ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ.ም ለንባብ አበቁ፡፡ መጽሐፉ ትውልድን እንደ እርሳስ የሚቀርጽ ነበርና የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያም ኾነ።
ብላታ መርስዔ ኀዘን በ1935 ዓ.ም “የአማርኛ ሰዋሰው”የተሰኘ የተማሪ መማሪያ መጽሐፍም አበረከቱ፡፡ይህ መጽሐፍ ለግማሽ ምዕት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሰዋሰው ማስተማሪያ ኾኖም አገልግሏል።
እኝህ የቋንቋ ሊቅ ሚያዝያ 1936 ዓ.ም “የብላታ” ማዕርግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በብላታ መርስዔ ኀዘን ከተደረሱ በርካታ መጻሕፍት ጥቂቶቹን ለቅምሻ እናስታውስዎ፡፡ ትምሕርተ ሕፃናት፣ የአማርኛ ሰዋሰው፣ የቤተ ክርስቲያን ጸሎት፣ የቤተ ክርስቲያን ዜና፣ የትእምርተ መንግሥት ታሪክ፣ ዐውደ መዋዕል፣ የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝ እና በአማርኛ፣ ቅዳሴ በእንግሊዝኛ ትርጉም ይገኙበታል፡፡
መርስዔ ኀዘን በ1922 ዓ.ም ወደ ጅግጅጋ ከተማ ተዛውረውም ለልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመኾን አምስት ዓመታት አገልግለዋል። በዚሁም ጊዜ ከተሰጣቸው ሥራዎች በተጨማሪ ውስጥ በወሰን ማካለል ሥራ ላይ ከወሰን ተከላካዮች ጋር የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ በዚህም ከ1924 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን ክልል ኮሚሽን እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ በዋና ጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡
ፋሽስት ጣልያን በኡጋዴን በኩል በወልወል ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም አደጋ ሲጥል መርስዔ ኀዘን በስፍራው ኾነው አደጋውን ተጋፍጠዋል፡፡
መርስዔ ኀዘን ከጽሕፈት ሥራቸው በተጨማሪም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ የታሪክ እና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር፣ የፍርድ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር፣ የታሪካዊ ቅርሶች አሥተዳደር አማካሪ፣ የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም በመኾን የተሰጣቸወን ግዴታ ተወጥተዋል፡፡ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ኾነውም ሠርተዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የቦርድ ሊቀ መንበርም ነበሩ፡፡
ድርሳነ ታሪክ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ በ1964 ዓ.ም ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ላበረከቱት ሰው ተኮር ሥራ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ኾኑ። እኝህ ሊቅ ሀገራቸውን ለ49 ዓመት ከሁለት ወር በቅንነት እና በታማኝነት አገልግለዋል። ነሐሴ 9/1971 ዓ.ም በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
👉 የመጀመሪያው አውሮፕላን
አሜሪካውያኑ ዊልበር እና ኦርቪል ራይትስ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ወንድማማቾች በራሳቸው ወጭ ነድፈው የሠሩትን በራሪ መሳሪያ በአሜሪካ ኪቲ ሃውክ ሰሜን ካሮላይና ወንዝ ዳርቻ ላይ አበረሩት።
ይህ በትንሽ የገጠር መንደር ውስጥ የተወጠነው አውሮፕላን ዛሬ ላይ በዓለም እጅግ በመዘመን ከድምጽ እስከ መፍጠን ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያም የመጀመሪያው አውሮፕላን በ1921 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ አርፏል፡፡ ይህ አውሮፕላን ከአየር ላይ እንደ አሞራ ዝቅ እያለ ሲመጣ በቦታው የነበረው ኢትዮጵያዊ በግርምት እና በትዕንግርት ይመለከቱ ነበር።
በሰላም እንዳረፈም ሁነቱን የተከታተለው ሕዝብ :-
‹‹ከቶ ምን አሳየኝ ይሠሩትን ያጡ፣
ጠንቀቅ! በል ጌታዬ ወደ አንተም ጋር መጡ፡፡››
በማለትም መልዕክታቸውን ለፈጣሪ አድርሰዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መንገድ ሳይሠራለት እና ሐዲድ ሳይነጠፍለት በአየር ላይ ተንሳፎ የመጣውን ያን አውሮፕላን “የአየር ባቡር” የሚል ስም አወጣለት፡፡
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴም የአውሮፕላኑ ስሪት ፈረንሳይ በመኾኑ እና ከሀገሪቱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመመሥረታቸውም አውሮፕላን በግዥ እንዲመጣላቸው ጠየቁ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም የፈረንሳይ መንግሥት ሦሥት ፖቴዝ አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ በጅቡቲ በኩል ላከ፡፡
አንደኛውን አውሮፕላንም ፈረንሳዊው ፓይለት ሙሴ አንድሬ ማዬ ከጅቡቲ ተነስቶ በማብረር ነሐሴ 8 ቀን 1921 ዓ.ም “ሥጋ ሜዳ” አውሮፕላን ማረፊያ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ላይ አሳረፈው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም አውሮፕላኑን እንደተረከበ “ንስረ-ተፈሪ” የሚል ስያሜ ቼረው፡፡
ቀሪዎቹ ፖቴዝ አውሮፕላኖች ደግሞ በካፒቴን ማዬ እንዲሁም በጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እየበረሩ መስከረም 1921 ዓ.ም አዲስ አበባ አረፉ፡፡
ሁለተኛው ፖቴዝ አውሮፕላንን የኢትየጵያ መንግሥት “ንስረ-አስፋወሰን” በሚል ሰየመው፡፡ ሦስተኛው ፖቴዝ አውሮፕላን ደግሞ “ንስረ-መኮንን” የሚል የመታዎቂያ ሥም ተሰጠው፡፡
ፈረንሳይ እና ጀርመን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ1884 ጀምሮ አፍሪካን በቅኝ ለመግዛት ይፎካከሩ ነበርና ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ መንግሥት አውሮፕላን ማቅረቧን አልወደደችውም፡፡
የፈረንሳይ አውሮፕላኖች አዲስ አበባ መግባታቸውን ተከትሎም የጀርመኑ ጀንከርስ አውሮፕላንም በባሮን ሻን ኢግል አብራሪነት ጃን ሜዳ አረፈ፡፡ ታዲያ አዲስ አበቤዎች ከፈረንሳዮች አውሮፕላን በበለጠ የጀርመኖችን አገኙ፡፡
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ የተጀመረው በፈረንሳይ አውሮፕላኖች እና ባለሙያዎች ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሀገር ውስጥ በረራም በጀርመኑ ጀንከርስ አውሮፕላን የኢሊባቡሩን ጠቅላይ ገዥ ራስ ናደው በጽኑ ታመው ነበርና የሚተኙበትን አልጋና ፍራሽ ጨምሮ ወደ ዋና ከተማቸው ጎሬ በረረ፡፡ ነገር ግን በአየር ሁኔታው አመቺ አለመኾን ምክንያት ተመልሶ እንድብር አካባቢ ለማረፍ ተገደደ፡፡ በማግስቱም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡
በዚህ ሁኔታው የተጀመረው የኢትዮጵያ አውሮፕላን በረራ በ1922 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የመጀመሪያው የአውሮፕላን በረራ ትምህርት ቤት በፈረንሳዊው ሙሴ ጋስቶን ቨርዲየር መምህርነት በሁለት አውሮፕላኖች ተቋቋመ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን የአውሮፕላን በረራ ሠልጣኞችም አስፋው አሊ፣ ሚሽካ ባቢችፍ፣ ስዩም ከበደ፣ ባህሩ ካባ፣ ደምሴ ኃይለኢየሱስ፣ ደመቀ ተክለወልድ እና የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አውሮፕላን አብራሪ ወይዘሮ ሙሉመቤት እምሩ ናቸው፡፡ወይዘሮ ሙሉመቤትን የአሜሪካ ጋዜጣ “ስናፒ ላንዲንግ ሌዲ በርድ” በሚል አድናቆት ታሪካቸውን ከትቧል፡፡
አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተማ ያረፈው በነሐሴ ወር 1921 ዓ.ም ነበር ሲል ያስነበበው ኢትዮጵያ ኤኒቲንግ ዶት ኮም ነው፡፡
👉 የፓናማ ቦይ መከፈት
በዓለም ላይ ሁለት ትልልቅ የሰው ሠራሽ ቦዮች ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ቀይ ባሕርን ከሜዲትራኒያን ባሕር የሚያገናኘው የስዊዝ ቦይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አትላንቲክ ውቅያኖስን ከፓስፊክ ውቅያኖስ የሚያስተሳስረው የፓናማ ቦይ ይሰኛል፡፡
ይህ ቦይ 82 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲኾን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 400 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቷል፡፡ ታዲያ ቦዩ ለመርከብ ጉዞ ክፍት መኾኑን ያበሰረችው የዩኤስ ቬስል አንኮን የተሰኘችው መርከብ ናት፡፡
በፓናማ ቦይ በኩል በቀን ከ60 በላይ መርከቦች ይተላለፉበታል፡፡ ከዚህም ፓናማ በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር የመስመር ኪራይ ታገኝበታለች፡፡ ታዲያ
ሁለቱን አህጉራት የሚከፍለው ይህ ቦይ ለባሕር ላይ መጓጓዣ በይፋ ክፍት የኾነው ልክ በዚህ ሳምንት ነሐሴ 9/1906 ዓ.ም እንደነበር ዚስ ዴይ ኢን ሒስትሪ አሰነብቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!