
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ድርሻ ካበረከቱ መሪዎች መካከል እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ እነዚህን መሪዎች መዘከር እና ማስታወስ ከትውልዱ ይጠበቃል።
የ180 ዓመት የእምዬ ምኒልክ የ184ኛ ዓመት፣ የእትጌ ጣይቱ ብጡል እና የፊታውራሪ ገብርዬ ካሳ የልደት ዝክረ በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
የልደት ዝክረ በዓሉ በደብረ ብርሃን ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት እና በሴት መሪዎች ፎረም የተዘጋጀ ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ “ዛሬ ላይ ኾነን ልደታቸውን የምንዘክራቸው እምዬ ምኒልክ እና እትጌ ጣይቱ በዓለም መድረክ ቀና ብለን እንድንሄድ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል።
መሪዎቹ ሀገር በሥልጣኔ ማማ እንድታልፍ ከማድረግ ባለፈ ጠላት እንዳይደፍራት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ብለዋል።
የዛሬ መሪዎች ከእምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ጽናትን ልንማር ይገባል ያሉት አቶ ወርቃለማሁ በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ያጣነውን ሰላም ለማረጋገጥ የቀደሙትን የጀግኖቹን መሪዎች ጥበብ እና ብልሃት ልንጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
የደብረብርሃን ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ላቀች ንጉሴ “ይህንን በዓል ስናከብር የነሱን ፈለግ በመከተል እና ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በመዘከር ሊኾን እንደሚገባም” አንስተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ቅመም አሽኔ እምዬ ምኒልክ እና እትጌ ጣይቱ ሀገራቸው ነጻነቷን እንድታገኝ በማድረግ ረገድ የሠሩትን ተጋድሎ ወጣቱ ትውልድ በውል በመገንዘብ የሀገርን ሰላም እና አንድነት ለማጽናት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡።
በልደት ዝከረ በዓሉ ላይ ወጣቶች፣ መሪዎች እንዲሁም የታሪክ ምሁራን ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!