3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሠብሠብ እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

18

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተያዘው የግብር ዘመን 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሠብሠብ አቅዶ አየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።

በክልል ደረጃ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በግብር አሠባሠብ ሂደቱ ላይ ጫና ቢፈጥርም በአንጻሩ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ግብር እየተሠበሠበ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ፈጠነ ጥላሁን ገልጸዋል።

በአሥተዳደሩ ደረጃ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተጣራ መረጃ ለመያዝ አንዳሰቸገረ የተናገሩት ምሪያ ኀላፊው፤ ሰላም በአለባቸው ወረዳዎች 13 ሺህ 330 ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

አነዚህ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብለዋል። ዚገም እና ጓንጓ ወረዳዎች የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ሙሉ በሙሉ ከፍለው አጠናቅቀዋል ብለዋል።

ባንጃ ወረዳ እና ቻግኒ ከተማ አሥተዳደር 70 በመቶ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን ማስከፈል ችለዋል ያሉት አቶ ፈጠነ አገው ግምጃ ቤት፣ እንጅባራ ከተማ አሥተዳደር፣ አዮ ጓጉሳ እና አንከሻ ወረዳ በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ ግብራቸውን ያልሠበሠቡ ናቸው ብለዋል።

እስከ አኹን ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መሠብሠብ የተቻለው 70 ሚሊዮን ብር ብቻ መኾኑን የገለጹት መምሪያ ኀላፊው ይሄ የተሠበሠበውም ሰላም ባለባቸው ቀጣናዎች መኾኑን ነው የተናገሩት።

ዳንግላ ዙሪያ ወረዳ እና ዳንግላ ከተማ አሥተዳደር፣ ጃዊ ወረዳ እና ፈንድቃ ከተማ አሥተዳደር፣ ጓጉሳ ሸኩዳድ እና ቲሊሊ ከተማ አሥተዳደር፣ ፋግታ ለኮማ እና አዲስ ቅዳም ከተማ አሥተዳደር በሰላም አጦት ምክንያት የአለፈው ዓመት እና የዘንድሮ ዓመት ግብር ያልተሠበሠበባቸው አካባቢዎች መኾናቸውንም መምሪያ ኀላፊው አብራርተዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የደረጃ “ለ” 1 ሺህ 141፣ የደረጃ “ሀ” 1 ሺህ 383 ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ፈጠነ ከእነዚህ ግብር ከፋዮች ግብር በወቅቱ ለመሠብሠብ ታቅዷል ነው ያሉት።

በተያዘው ግብር ዘመን ከመደበኛ የገቢ አርዕስቶች 2 ቢሊዮን 326 ሚሊዮን 979 ሺህ ብር በላይ ግብር ለመሠብሠብ ታቅዷል ያሉት መምሪያ ኀላፊው መደበኛ ያልኾኑ ከአግልግሎት ዘርፎች 822 ሚሊዮን 664 ሺህ ብር በላይ ይሠበሠባል ብለዋል።

በሁለቱም የገቢ አርዕስቶች 3 ቢሊዮን 148 ሚሊዮን 643 ሺህ በላይ እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብር ለመሠብሠብ መታቀዱን ገልጸዋል።

የታቀደውን ግብር መሠብሠብ የሚቻለው በኹሉም አካባቢዎች ሰላም ሲረጋገጥ መኾኑን ያነሱት አቶ ፈጠነ ጥላሁን ኹሉም አካል ቅድሚያ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።

መምሪያ ኀላፊው የኹሉም ደረጃ ግብር ከፋዮችም በወቅቱ የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ከቅጣት መዳን እንዳለባቸው መልዕክት አሥተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ስንታየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያልተከበሩት እሴቶቻችን
Next article“አጼ ምኒልክ እና እትጌ ጣይቱ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ እንድትል ያደረጉ መሪ ናቸው” ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ