
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳደረባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች (ፋይንቴክ) ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ለአካታች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ወሳኝ መኾኑንም ኩባንያዎቹ ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ ለኢንቨስትመንት ዝግ የነበሩ መስኮች ክፍት እንዲኾኑ ተደርጓል ነው ያሉት።
ለአብነትም በውጭ ምንዛሬ አሥተዳድር የተደረገው ማሻሻያ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ለውጭ ተቋማት ክፍት እንዲኾን መወሰኑ ባንኮችን ጨምሮ የፋይናንስ ዘርፍ ተዋናዮችን ቀልብ እየሳበ መጥቷል።
የፋይናንስ ተቋማቱ ቴክኖሎጂ አቅራቢ እና አማካሪ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ በፖሊሲ ማሻሻያ ላይ የወሰደቸው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል ”ፊናክል ሶሉሺን” የተሰኘው የሕንዱ ዓለም አቀፍ የባንክ አማካሪ ኩባንያ ኀላፊ ናሬሽ ብሀኖትራ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለምጣኔ ሃብቷ ዘላቂ እድገት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።፡፡
የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ በር የሚከፍት እና ለሀገር በቀልና ለውጭ ፋይናንስ ተቋማት የጋራ ትብብር፣ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።
በፋይናንስ ተቋማት ትስስር ላይ የሚሠራው የዓለም ስትራቴጂክ ጥምረት ማዕከል የስትራቴጂ ትብብር ኀላፊ መሐመድ ቶፊቅ በርካታ ታዳጊ ሀገራት ያደረጉት የፖሊሲ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዕድገት ምህዋር ኾኗቸዋል ይላሉ።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንስተዋል።
መሠረቱን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የ”ኢ ኤፍ ቲ” ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላይተን ሀይዋርድ ኩባንያው ለዲጂታል ባንክ አገልግሎት የሚበጁ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርብ መኾኑን አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ መፈቀዱ ለአካታች ፋይናንስ ሥርዓት ትግበራ ትልቅ ትርጉም ያለው መኾኑን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች ታግዘው በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ያደርጋል ብለዋል።
በአብዛኛው የዓለም ሀገራት አገልግሎት የሚሰጠው ኬንያ በቀሉ የ”ካስፐርስኪ” ዓለም አቀፍ የዲጂታል ባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ሽያጭ ኀላፊ ቤተል ኦፒል ይህን ሃሳብ ይጋራሉ።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት እና ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለድርሻ አካላት ክፍት ማድረጓ ኩባንያዎቹን በመሳብ ዘርፉ አካታች እና ተደራሽ እንዲኾን ያስችላል ብለዋል።
‘ኪኤምፒጂ” የተሰኘው ሌላው የባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ዳይሬክተር ማቲን ኪማኒ የአፍሪካ ሀገራት በትስስር እንጂ በተናጠል ዘላቂ ዕድገት ማምጣት የማይችሉ መኾኑን አንስተዋል።
በመኾኑም ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ያደረገችው ማሻሻያ የዓለም ኩባንያዎችን ቀልብ የሚስብ እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እምርታም መሠረት የሚጥል መኾኑን ገልጸዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ ተቋማት የበለጠ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ድንበር ዘለል ተደራሽነት እንዲያሰፉ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ኩባንያዎቹ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የዘርፉ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በተለይም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!