
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን የዞን፣የወረዳና የከተማ አሥተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ኃላፊዎች የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ የውውይት መርሐ ግብር በፍኖተ ሰላም ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የፍኖተ ሰላም አተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሙሉጌታ አለም በከተማ አሥተዳደሩ የገጠመውን የፀጥታ ችግር ከሰላም ወዳደዱ ሕዝብና ጥምር ኀይሉ ጋር በፅናት በመሻገር በከተማ አሥተዳደሩ አንፃራዊ ሰላም ተፈጥሯል ብለዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም አሁን መደመኛ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ነው ምክትል ከንቲባው የገለፁት።
የፍኖተ ሰላም ከተማ ለኢንቨስትመት የተመቸችና ታታሪ ሕዝብ ባለቤት በመኾኗ ይህን አቅም በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል
ፍኖተ ሰላምን በአግባቡ በማልማት ሕዝቡን ከገጠመው ችግር ለማሻገር አመራሩ በቂ ዝግጁ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ያሳለፍነው ዓመት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ችግር የዞኑ ሕዝብ ከፍተኛ የደኅንነት አደጋ ውስጥ ገብቶ መቆየቱን አውስተዋል።
በዞኑ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም መጥቷል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፀጥታ ኀይሉና መሪዎች ሕዝቡን በማስተባበር በተሠሩት የሰላምና ፀጥታ ሥራ የተገኘ ስኬት መኾኑን ተናግዋል።
ዞኑ አሁን ላይ እየሠራ ካለው የሰላምና ፀጥታ ሥራ ጎን ለጎን ሕዝቡ አጥብቆ የሚሻውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ማለታቸውን ከምእራብ ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል፣ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ማሳለጥና ሕገ ወጥነትን መከላከል የዚህ ዓመት ቁልፍ ተግባር መኾኑንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!