በክረምት በጎ ፈቃድ የማጠናከርያ ትምህርት በተጠናከረ መንገድ እየተሰጠ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

24

ሰቆጣ: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተጠናክሮ የቀጠለ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

በጎ አድራጊ ወጣቶች በመንገድ ጥገና፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን እና የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ ብሏል ትምህርት መምሪያው።

በክረምት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት በቀጣይ ዓመት ለሚያደርጉት የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ለመዘጋጀት እንደሚረዳቸው ሀሳባቸውን ያጋሩን የጻግቭጂ ወረዳ የጻታ ከተማ ተማሪዎች ተናግረዋል።

የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ከሚወስዱት መካከል ተማሪ ትጉህ ብርሃኑ አንዱ ሲኾን ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች የሚሰጡት ድጋፍ ለተማሪዎች የሚመጥን እንደኾነ ገልጿል። ባለፈው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች የታለፉ የትምህርት አይነቶችን እየሸፈኑላቸው መኾኑንም ነው የገለጸው።

በአዲሱ ዓመት የምንወስዳቸውን የትምህርት አይነቶች መማራችን ቀጣይ የክለሳ ያክል እንድንማረው ያግዘናል ያለችው የ10ኛ ክፍል ተማሪ መቅደስ አታሌ አስተማሪዎቹም ዩኒቨርሲቲ ላይ በተሻለ ውጤት ያጠናቀቁበትን ልምድም አካፍለውናል ብላለች።

ባለፈው ዓመት በጻግቭጂ ወረዳ 97 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መውደቃቸው በክረምት መርሐ ግብር የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሠጡ እንዳነሳሳቸው ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የተመረቀው አቤል ሽምኑ ተናግሯል።

በቀጣይ ዓመት ቢቻል ኹሉም ካልኾነ ግን 97 በመቶው እንዲያልፉ ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር በክረምት በጎ ፈቃድ እያስተማሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

በጻግቭጂ ወረዳ በክረምት በጎ ፈቃድ የማጠናከርያ ትምህርት በ4 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተሰጠ መኾኑን የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደሩ ተሻለ ተናግረዋል። በዚህም 360 ተማሪዎች የአገልግሎቱ ተሳታፊ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ለሚያስተምሩ በጎ አድራጊ ወጣቶችም የግብዓት ድጋፍ ያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የክረምት በጎ ፈቃድ የሚሰጠው የማጠናከርያ ትምህርት ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፈ ሞገሥ ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 29 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ለ2ሺህ 63 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደኾነ የገለጹት ሰይፈ በ7 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 259 ተማሪዎች እየተማሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የክረምት በጎ ፈቃድ የሚያስተምሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ያመሠገኑት ሰይፈ ለአዲሱ የትምህርት ዘመንም ከወዲሁ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:-ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” የታሪክ ማሕደር፤ የውበት መግቢያ በር”
Next article“ክልሉ ካጋጠመው ቀውስ በፍጥነት ለመውጣት የቁጭት እቅድ አዘጋጅቷል” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)