
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ደመና ያዘለው ሰማይ እንደከበደ ነው። ከጨለማ ጋር ተባብሮ ብርሃንን አልገልጥም ያለ ይመስላል። ምድር ከእንቅልፏ አልነቃችም። የሚያዋክቧት ድምጾች፣ ሰላምን የሚነሱት ጫጫታ እና ሁካታዎች አይሰሙም። በማለዳ የሚናፈቁት አዕዋፋት እንኳን መዘመር አልጀመሩም። የክረምት ቆፈን ይዟቸው፣ ወይንም ቦታ ቀይረው ሰው ወደ ማይኖርበት አካባቢ ሄደው ይኾናል ያማረ ኅብረ ዝማሬያቸውን አያሰሙም።
ሰማዩ በጠቆረ ደመና ተሸብቧል። ጀምበር ላትመለስ ተሰናብታ የጠለቀች እንጂ በማለዳ በምሥራቅ የምትዘልቅ አትመስልም። ደመና ያዘለው ሰማይ እና ድቅድቅ ጨለማ ተባብረው የምሥራቅ በሯን የከረቸሙባት ይመስላሉ። በማዕልት እርሷ ትነግሣለች፣ በሌሊት ዙፋኑን ለጨለማ አስረክባ ወደ ማደሪያዋ ትገባለች። በዚያ ቀን ግን ላትመለስ በሯን የከረቸመች፣ ወደ ንግሥናዋም ላለመመለስ የቆረጠች ትመስላለች።
ማን ይኾን ግን ወደ መኝታው ሲሄድ ጀምበር ሳትመለስ ብትቀር ምን እንኾናለን ብሎ አስቦ የሚያውቅ? ምድር በጨለማ ካባ እንደተጠቀለለች ብትቀር ማስለቀቅ የሚቻለው ፍጡርስ ይኖር ይኾን? ብቻ ሁሉም ብርሃን እና ጨለማ ሲፈራረቁ እያየ ይኖራል። ሁካታ የበዛባት፣ እረፍት የታጣባት ምድር እፎይ ብላ ተኝታ ላለመነሳት የቆረጠች በምትመስልበት በዚያ ሰዓት ከአልጋዬ ተነስቼ በረጋች ምድር ያለውን ሁሉ እቃኝ ጀመር።
ደመና ያዘለው ጥቁር ሰማይ የከበደ መደረቢያውን አላነሳ ብሎ እንጂ የሌሊቱ ጊዜ አልቆ ኖሯል። እንደወትሮው ቢኾን ኖሮ ጀምበር በምሥራቅ ንፍቅ ልትፍለቀለቅ ስትታትር ትታይ ነበር። ደመና ያዘለው የክረምት ሰማይ ግን በደመና ጠቅልሎ ምድርን ውበቷን ጋረደባት። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ጥቁሩ ሰማይ ተረታ። ብርሃን እያሸነፈው መጣ። የጨለማውን መሸነፍ፣ የብርሃኑን ማሸነፍ ያየ ሁሉ ምናለ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተጋረደው የግጭት እና የጠብ ጥቁር ደመናም ጥቅልል ብሎ በጠፋ ማለቱ አይቀርም። መከራ በበዛበት ጥቁር ዘመን መኖር ይሰለቻልና።
የጣና በረከት፣ የግዮን ውበት የማይለያት ባሕር ዳር በማለዳ ያረፈባት ጭጋግ ባዘቶ የመሰለ ጋቢ የለበሰ አዛውንት አስመስሏታል። ባማሩ ጎዳናዎቿ ሲመላለሱ የሚታይ ሰው አልነበረም። እንዲያ ንጋት እና ጨለማ ባለየበት ማለዳ ብርቱ ጉዳይ ነበረኝ። በማለዳ ከቤቴ ወጥቼ በምስጢር ወደ ተመላው ጣና ሐይቅ ዳርቻ ገሰገስኩ። የጣና ሐይቅን አቋርጣለሁ። በጣና ሐይቅ የልብ ራስ በምትገኝ ታሪክ በበዛላት፣ ሃይማኖት በጠበቃት፣ ውበት በተቸራት ሥፍራ ለመገኘት።
አብረውኝ የሚጓዙት ባልንጀሮቼ በማለዳ በጣና ዳርቻ ተገኝተዋል። ጀምበር ደመናውን ጥሳ ለመውጣት የምትታገል ትመስላለች። ከባሕር ዳር ጫፍ ወደ ጣና ልብ ራስ የምትወስደን ጀልባ መልሕቋን ዘርግታ ቆማለች። የእኛን መምጣት ነበር የምትጠባበቀው። ጀልባዋ ጣናን በፍጥነት እያቋረጠች የምትጓዝ ዘመናዊት ናት። በጣና ዳርቻ ተሠባሠብን። በማለዳ የጀልባዋን መልሕቅ ዘርግቶ ሲጠብቀን የነበረው ካፒቴን ወደ ጀልባዋ እንገባ ዘንድ ጋበዘን። ወዲያው የጀልባዋን መልሕቅ ሠበሠበ። መልሕቋን ሠብሥቦ የጀልባዋን ፊት አዙሮ ጣናን ይከፍለው ጀመር።
ጣና ሐይቅ ውኃ ብቻ አይደለም የሞላበት፣ አሳዎች እና ጉማሬዎች የበዙበት። ጣና ውኃ ብቻ አይደለም ታጥበው የሚነጹበት፣ ጠጥተው የሚረኩበት። ጣና ከውኃነት ያልፋል። ከሐይቅም ይገዝፋል። ጣና ብራና ነው ታሪክ የሚነበብበት፣ ብዕር ነው የዘመናት ጥበብ የሚጻፍበት፣ ጣና ዋሻ ነው ቅዱሳን አበው የሚጠለሉበት፣ ጣና ቁልፍ ነው የተዘጉ የዘመናት በሮች የሚከፈቱበት፣ ጣና መስታውት ነው ትናንት እና ዛሬ የሚታይበት፣ ጣና ትንቢት ነው ነገ የሚነገርበት፣ ጣና ቃል ኪዳን ነው ትውልድ ሁሉ የሚማማልበት፣ የሚተሳሰርበት፣ ጣና ኑሮ ነው እንጀራ የሚቆረስበት፣ ጣና ኩራት ነው ቀዳሚነት፣ ጥንታዊት የሚገለጥበት።
ፈጣኗ ጀልባ ሐይቁን እየሰነጠቀች ገሰገሰች። ዓይኔ ዙሪያ ገባውን ይቃኛል። የጣና ገዳማት በጥቅጥቅ ደን ተሸፍነው ይታያሉ። ባሻገር የሚያያቸው ውበታቸውን፣ ግርማቸውን እና ሞገሳቸውን ያደንቃል። ውስጣቸውን የተመለከተ ግን በጥበባቸው ይደነቃል። እኒያ የሐይቅ ውስጥ ገዳማት ታይተው አይጠገቡም። ቢነገርላቸው፣ ቢዘመርላቸው፣ ቢጻፍላቸው መግለጽ አይቻልም። ግሩም ድንቅ እያሉ ማለፍ ካልኾነ በስተቀር። የያዙት እጹብ ድንቅ ነውና። በጣና ሐይቅ ባለፍኩ ቁጥር የዓባይ እና የጣና ነገር ይገርመኛል።
” ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት
ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት” እንዳለ የሀገሬው ሰው ዓባይ በጣና ላይ ይሄዳል። ውኃ በውኃ ላይ አልፎ ሲሄድ ማየት እንዴት ይደንቅ?
ጀምበር ድል አድርጋለች። ሰማይን የጋረደው ጥቁሩ ደመና የት ተጠቅልሎ እንደገባ ባይታወቅም ከነበረበት ጠፍቷል። ጀምበር በእልፍ አጃቢዎች ተከባ፣ በሠረገላ ላይ ተቀምጣ፣ ዓይነ እርግቧን ከፍታ የምትወጣ ልዕልት ትመስላለች። የማለዳ ውበቷ ያስደስታል። ጀልባዋ ሐይቁን እየሰነጠቀች፣ በግራና በቀኝ አምረው የሚታዩትን ገዳማት እያለፍን ወደፊት ገሰገስን። ደስ ከሚል ጉዞ በኋላ መዳረሻችንን በሩቅ ማየት ጀመርን። በአሻገር ሲያዩዋት ታሳሳለች። በአሻገር እያሳሳችን፣ በውበቷ እየጠራችን፣ ኑ ቅረቡ፣ በውበቴ ላስውባችሁ፣ በግርማዬ ላስደስታችሁ እያለችን ቀረብናት። ጀልባዋ መልሕቋን ዘረጋች። ሩጫዬን ጨርሻለሁ አለች። ከጀልባዋ እየወረድን ገና በአሻገር ኑ እያለች የጠራችንን የውበት ገምቦ አገኘናት።
መዳረሻችን ዘመን ያከበራት፣ ዘመንም የሸፈናት፣ መልሶም የገለጣት ከውበት ውበት፣ ከታሪክ ታሪክ ተመርጦ የተሰጣት፣ የመወደድ ግርማ የተቸራት ናት። አበው ከረጅም ዘመናት በፊት መረጧት፣ እንደ ተራራ የገዘፈውን፣ እንደ ዥረት እየፈሰሰ የሚነገረውን የከበረውን ታሪክ አከማቹባት፣ የረቀቀውን አሻራ አስቀመጡባት ጎርጎራ።
ያቺ ውብ ሥፍራ ጎርጎራ ገና ጥንት ዘመን እንደገለጣት ዘመንም ሸፍኗት፣ ትውልድ ዘንግቷት ፣ የተከበረውን ታሪኳን ሸሸጎባት ኖረ። ውበቷን ደብቃ እርሷን አብርታ የምታሳይ ጀምበር እስክትወጣ ድረስ ጠበቀች። ጠብቃም አልቀረች። እርሷን የምታሳየው ጀምበር ወጣች። ታሪኳን ገለጠችላት፣ ውበቷን አሳየችላት። ያተመችውን ደም ግባት አፈካችላት። አሁን ከቤተ መንግሥት እንደተቀመጠች፣ በእንቁ እንዳጌጠች፣ በአልማዝ የተዋበ ካባ እንደደረበች፣ የወርቅ መጫሚያ እንዳደረገች፣ በነበልባል ሠረገላ ላይ ተቀምጣ ሕዝብን እየቃኘች እንደምትታይ ንግሥት መስላለች። አሁን የተረሳችው የሚያስታውሳት አግኝታለች፣ ያንቀላፋችው ተነስታለች።
የጎርጎራ ታሪክ ከ700 ዓመታት በፊት ከተገደመችው ከደብረ ሲና ማርያም ጋር ይጣቀሳል። ንጉሡ ዓምደጽዮን ያቺን ጥንታዊት ገዳም በእሣር ክዳን አስውበው ባስገደሟት ጊዜ ጎርጎራም በዚያ ዘመን እንደተመሠረተች ይነገራል። ታላቁ ንጉሥ ዓምደጽዮን ስማቸው የሚወሳበትን፣ ታሪካቸው የሚነገርበትን አያሌ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል። ደብረ ሲና እና ጎርጎራ በተነሡ ቁጥር እርሳቸውም ይነሳሉ።
ጎርጎራ ተወልደው ያደጉት መቶ አለቃ የሺዋስ አበራ ጎርጎራ ገዳማት የሚከቧት፣ ታሪክ የሞላባት፣ ሃይማኖት የጸናባት ጥንታዊት ከተማ ናት ይሏታል። ጣና እንደመቀነት ይደግፋታል፣ እንደመስታውትም ውበቷን ያሳያታል፣ ተፈጥሮ አድሏታል፣ ዓይኖች ሁሉ አይተው የማይጠግቧት ውብ ናት ይላሉ። እርሷ እንኳን የተወለዱባት፣ አፈሯን ፈጭተው፣ ጭቃውን አቡክተው፣ ከምንጯ ጠጥተው ያደጉባት የውጭ ሀገር ሰዎችም ይናፍቋታል። አንልቀቅሽ ይሏታል ነው የሚሉት።
ጎርጎራ መንፈሳውያን እንደተጠበቁ፣ ታሪኳ እና ሃይማኖቷ ሳይነካ፣ በሐይቁ ዳርቻ ወታደሮች የጦር ሠፈር አድርገዋት ይኖሩ እንደነበርም ከታሪኳ ይመዛሉ። ይህም በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ በደርግ ዘመንም ነበር። ዛሬም ድረስ በጎርጎራ ከኢትዮጵያ ክፍላተሀገር የተገኙ የኢትዮጵያ የቀድሞ ወታደሮች እና የወታደር ልጆች ይገኙባታል። በዚያች ምድር ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ይታወቃሉ። ኢጣሊያ ለወረራ መጥታ በነበረበት ጊዜም ወታደሮቿን በጎርጎራ አሥፍራ እንደነበርም ይነገራል። አርበኞች እንደ እግር እሳት እየለበለቡ አላስቀምጣት ብለው ነበርና ከጎርጎራ ራስጌ ካለው ተራራ ላይ ሐውልት ሠርታ በሩቅ የሚመጡትን አርበኞች ትመለከትበት እንደነበር ይነገራል። ያ ሐውልት ዛሬም ድረስ ቆሟል።
ታሪክ አዋቂው ሙሉቀን ሽባባው ጎርጎራ ታላቋን ደብረ ሲና ማርያምን፣ የአጼ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥትን እና ሌሎችን አያሌ ታሪኮችን የያዘች ጥንታዊት ሥፍራ ናት ይሏታል። ታሪኳ፣ ባሕሏ፣ ሃይማኖቷ ከእነ ክብራቸው የቆዩ ናቸው ይላሉ። ነገሥታቱ ያርፉባት፣ በየገዳማቱ እየገቡ ይጸልዩባት፣ ቅዱሳን አበው የቅድስና ታሪክ ይሠሩባት እንደነበር ይናገራሉ።
የጎርጎራ ነዋሪው ሻለቃባሻ ሰሎሞን በቀለ ጎርጎራ ከደብረ ሲና ማርያም ጥላ ሥር የምትኖር የበረከት ከተማ ናት ይሏታል። የልጅነት ትውስታቸውን ሲያስታውሱ በልጅነት ዘመኔ በጎርጎራ ወታደሮች ከትመውባት ይኖሩባት ነበር ይላሉ።
ጎርጎራ በዘመነ ደርግ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አይተዋት አሳምረዋት ነበር። የእርሳቸውም የሕልም ከተማ ነበረች ይባላል። የእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ከተፈጸመ በኋላ ግን ተከትሏቸው የመጣው ሥርዓት ጎርጎራን ፈጽሞ ረሳት። ያም አለፈና ሌላ ጊዜ መጣ። ጎርጎራ ከተደበቀችበት ተፈለገች። ታሪክ አዋቂው ሙሉቀን ሽባባው ከደርግ በኋላ በተረሳች ጊዜ ዝም ብላ ቆዬች። የመገፋት ብቻ ሳይኾን የመነሳት ዘመን እንደሚመጣ ታምን ነበር ይላሉ። አበው ቀደም ባለው ጊዜ ” ጎርጎራ ተጽዕኖ ይደርስባታል፣ ትረሳለች፣ በኋላ ግን ባልታሰበ ጊዜ ታድጋለች” እያሉ ይናገሩ ነበር። ያ ትንቢታዊ ንግግር አሁን የተፈጸመ ይመስላል ነው የሚሉት።
ጎርጎራ እንኳን እንዲህ አምሮባት፣ በተረሳችበት፣ በተቸገረችበት ዘመንም ጠብቀናታል፣ አብዝተን ወደናታል፣ ኖረንባታል። አሁን ደግሞ የበለጠ እንወዳታለን ፣ ጠብቀን ለመጭው ትውልድ እናስተላልፋታለን ነው ያሉት።
ሻለቃባሻ ሰሎሞን በቀለ ጎርጎራ ተረስታ፣ ተትታ፣ ተዳፍና ነበር፣ አሁን ተገለጠች ይሏታል። ይሄን የሠሩ ዕድሜ ይስጣቸው፣ ይሄን ሥራ አለማድነቅ፣ አለማመሥገን፣ ሠሪዎችን አለመመረቅ ንፉግነት ነው ይላሉ። መቶ አለቃ የሺዋስ አሁን ጎርጎራ ሁሉንም ትጠራለች፣ ከውበት ላይ ውበት ተጨምሮላታልና ነው የሚሏት። ሌላኛው የጎርጎራ ነዋሪ መልሰው ዳምጤ ጎርጎራ ከቀይ ባሕር ዳርቻዎች፣ ከጥንታውያን ወደቦች ጋር ትሥሥር ያላት፣ በቀይ ባሕር አልፎ የሚመጣው ወደ እርሷ የሚመጣባት የነበረች ናት ይሏታል።
” ጎርጎራ ጎርጎራ ስምሽ የተጠራ፣
ጣና መስታውትሽ ከፊት የሚያበራ” እየተባለ ሲገጠምላት ኖሯል። ጣና መስታውት ኾኖላት ኖሯል፣ አሁንም እያሳያት ነው፣ ድንቋ ምድር ናት፣ ከዚህ በኋላ ጎብኝ አይጠፋባትም ይሏታል። ፍቅር የመላባት፣ ደግነት የበዛባት ናት ጎርጎራ።
ከውበት ላይ ውበት የደራረበችውን ጎርጎራን ተመለከትኳት። ቃኘኋት። እጅግ አምራለች። ያን ውበት አለማድነቅ አይቻልም። በተለይም በተረሳችበት ዘመን የሚያውቃት በአሁኑ ውበቷ አብዝቶ ይደነቃል። ስለ ምን ቢሉ የጣና የልብ ቅርጹ ጫፋ ካረፈባት፣ ከውበት ላይ ውበት ከደራረበባት፣ እንደ እጅ መዳፍ የለሰለሰው የደምቢያ ምድር ካስጌጣት ውብ ሥፍራ ያማረ ነገር ተሠርቷልና።
አምረው በተሠሩት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እየተጓዝኩ፣ በግራና በቀኝ የተዋቡትን ጌጦች እያስተዋልኩ፣ በረጃጅም ዛፎች ሥር ለሥር እያለፍኩ በመዝኛ ሥፍራው ሀገር ያፈራውን እየተጎነጩ ዓለምን የሚቀጩ ዓለማውያንን፣ በደብረሲና ማርያም ገዳም የሚመላለሱ ገዳማውያን፣ መንፈሳውያንን በሕሊናዬ አሰብኳቸው። ሁሉም በየፈርጁ ያስደስታል። አንደኛው በዓለም ይደሰታል። ሌላኛው በመንፈስ ይመሰጣል። ግሩም ነው።
ከሐይቁ ዳር እስከ ኮረብታዎቹ ድረስ የተሠሩትን ውብ ሥፍራዎች ተመለከትኳቸው። ውበታቸው የሚደንቅ ነው። የጎርጎራን ውበት ሳልጠግባት ጀምበር ወደ መስኮቷ ገሰገሰች። እየሳሳሁላት ወደ ሐይቁ ዳር ወረድኩ። በሐይቁ ዳር መልሕቋን ዘርግታ የምትጠብቀኝ ጀልባ ነበረችና።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!