ከ16ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ መወጣታቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

26

ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ከልዩ ልዩ የገቢ አርዕስቶች ገቢ ለመሠብሠብ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልዕክ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ይህን ተከትሎም በዞኑ ከሚገኙ ስምንት ከተማ አሥተዳደሮች በሰባቱ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በሐምሌ ወር የግብር ግዴታቸውን እንደተወጡ የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ገነት በቀለ ተናግረዋል።

መምሪያ ኀላፊዋ በዞኑ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ግዴታቸውን ያልተወጡ ግብር ከፋዮች ውዝፍ እና የዘመኑን ግብር በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዞኑ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተጎዱ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እና የሕዝቡን የመልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በዞኑ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሠብሠብ ተገቢ እንደኾነም ገልጸዋል።

ለዚህም የዞኑ ግብር ከፋዮች ውዝፍ እና የዘመኑን ግብር በወቅቱ በመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን እስከ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ድረስ ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት 122 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሠብሠቡም ተገልጿል።

ከ16ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችም የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ መወጣታቸውን ነው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ያስታወቁት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ556 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next article“ለነሐሴ 17 እንዘጋጅ!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)