በመንግሥትና በሕዝብ ኃብት ላይ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መኾኑ ተገለጸ።

47

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በታክስ ሥወራ፣ በግብር ማጭበርበር፣ ያለደረሰኝ ግብይት በመፈጸምና ሐሰተኛ ማስረጃ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ፥ በታክስ ሥወራ፣ ግብር ማጭበርበር፣ ያለደረሰኝ ግብይትና ሐሰተኛ ማስረጃ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሀገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመመርመር ተገቢው የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የአሜሪካን ዶላር ለማውጣት የነበረውን ሙከራ በማክሸፍ እና የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ተጠርጣሪዎች ማረሚያ ቤት ወርደው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አንስተዋል።

በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ አሻጥሮችን በመቆጣጠር ፖሊስ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በመንግሥትና በሕዝብ ኃብት ላይ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በድምሩ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውንም ነው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ ያስረዱት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ሕዝቡ የአሉቧልታ ዘመቻው ትክክል አለመኾኑን ተገንዝቦ ወደ ሥራ እየተመለሰ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleየሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ከባቢ ይፈጥራል” አቶ አሕመድ ሽዴ