”ሕዝቡ የአሉቧልታ ዘመቻው ትክክል አለመኾኑን ተገንዝቦ ወደ ሥራ እየተመለሰ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

42

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎች የከተማዋን የጸጥታ እና የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

መሪዎቹ የከተማውን የትራንስፖርት እና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴንም ተዘዋውረው ተመልክዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የከተማዋን ሰላም መኾን በማይፈልጉ ቡድኖች ወሬ እና ፕሮፖጋንዳ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እና አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ሥራ የማቆም ሁኔታ ነበር ብለዋል።

በዕለቱም ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከአሽከርካሪ ማኅበራት፣ ከአመራሩ፣ ከጸጥታ መዋቅሩ እና ከልዩ ልዩ ድርጅቶች ባለቤቶች ጋር ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል። ውይይቱን መሠረት በማድረግም ሕብረተሰቡ ወደ መደበኛ ሥራ እየተመለሰ መኾኑን ገልጸዋል።

ባጃጆች፣ ታክሲዎች እና የመንግሥት ተቋማት ተሽከርካሪዎች መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ ነው፤ የንግድ ድርጅቶች ተከፍተው ሥራ ላይ ናቸው፤ እናም በከተማዋ መደበኛ ሥራ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመልሷል ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ሰላም ወዳድ እና ሠርቶ አዳሪ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሩ የተፈጠረው ኅብረተሰቡ የሚነዛውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብሎ ሳይኾን በስጋት እና ፍራቻ መኾኑን ገልጸዋል።

ዛሬ ግን በወሬ ተሸብሮ የሚዘጋ ከተማ መኖር የለበትም የሚለውን በመነጋገር እና በመተማመን ኅብረተሰቡ ወደ ሥራ መመለሱን አስረድተዋል።

ለዚህም ለመላው የከተማው ሕዝብ ምሥጋና አቅርበዋል። መሪዎች እና የጸጥታ ኀይሉ ችግሩን ለመቅረፍ ያደረጉት የጋራ ጥረትም የሚመሠገን ነው ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ ”ከተማችን አሁን ሰላም ናት፤ በተወራው ልክም ሳይኾን ጸጥታዋን የሚያውክ ነገር የለም፤ ሰላሙን እያወከው ያለው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ነው” ብለዋል።

”ሕዝቡ በወሬ የማሸበር እና የአሉቧልታ ዘመቻ ትክክል አለመኾኑን ተገንዝቦ በመቃወም ወደ ሥራ እየተመለሰ ነው” ብለዋል።

በቀጣይም ማኅበረሰቡ ሕግ እያስከበረ ያለ መንግሥት መኖሩን እንዲገነዘብ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተደናግሮ ሥራ ማቆም እንደሌለበት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።

ለሰዓታት እንኳ ሥራ ማቆም ምን ያህል እንደሚጎዳ ይታወቃል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መላው የከተማዋ ነዋሪ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች እና ባለቤቶች በወሬ ተደናግረው ከሥራ ውጭ መኾን እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡ በኑሮ ውድነት ጫና ውስጥ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ሥራ በመዝጋት ራስን ማዳከም ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።

”የአማራን ሕዝብ ሥራ አትሥራ ብሎ ሥራ በማስቆም ምን ሊመጣ የሚችል ለውጥ አለ?” ሲሉ የጠየቁት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ ‘ዝጉ! ክፈቱ!’ እያሉ ሕዝቡን ማደናገር እና መጉዳት ተገቢነት የለውም ብለዋል።

ኅብረተሰቡም ከመንግሥት ትክክለኛ መረጃ በመውሰድ፣ አዳምጦ እና መርምሮ እንጅ በሚናፈስ ወሬ መረበሽ እንደሌለበት ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ችግር እየፈጠሩበት ያሉ ኀይሎችን ‘ትክክል አይደለም’ ብሎ መቃወም ሲጀምር ‘ትዕዛዝ አልሰጠንም’ ማለት ጀምረዋል ብለዋል። ኅብረተሰቡ ወደ ሥራ ሲገባ መንግሥት እንዳስገደደ አድርገው የሚያናፍሱ መኖራቸውንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል።

ሁሉም የሚጎዱት ክልሉን፣ የባሕር ዳር ከተማን እና ሕዝቡን ስለኾነ ከተማዋን ለጉዳት ከሚዳርግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ለመታቀብ ኅብረተሰቡ አዳምጦ እና አስተውሎ፤ ትክክል ያልኾነውንም ትክክል አይደለም ብሎ መገሰጽ ተገቢ ይኾናል ብለዋል። የተጀመረው እንቅስቃሴም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ እና የታክስ አሥተዳደርን የሚዳስስ መጽሐፍ አስመረቀ፡፡
Next articleበመንግሥትና በሕዝብ ኃብት ላይ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መኾኑ ተገለጸ።