
አዲስ አበባ: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ እና የታክስ አሥተዳደርን የሚዳስስ መጽሐፍ አስመርቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ፣ በአድማስ፣ በጌጅ እና በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በታክስ እና ጉምሩክ ሕግ ዙሪያ ለሠለጠኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የምስክር ወረቀትን ሰጥቷል፡፡
መጽሐፉ በሚኒስቴሩ ሙሉ ወጭ የተሸፈነ መኾኑ የተገለጸ ሲኾን የታክስ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎችን ግብር ከፋዮች እንዲረዱ ታሳቢ በማድረግ በነጻ ለአንባቢያን የሚሰራጭ መኾኑም ተጠቅሷል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ሞራል ያለው ማኅበረሰብ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ መሠረታዊ የታክስ ሕግ ሥልጠና መሰጠቱ እና የግብር አከፋፈል ሕግን እና ደንብን የሚያስረዳ መጽሐፍ መታተሙ የግብር እና የታክስ ክፍያን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
የታክስ እና ግብር ሕጎችን በመረዳት ሴክተሩን ለማሳደግ ሁሉም በሥራ ድርሻው ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል ዳሬክተር በፍርዱ መሠረት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ስለ ታክስ እና ጉምሩክ ሕግ ሥልጠና መውሰዳቸው ሕግ አክባሪ እንዲኾኑ እና በኀላፊነት ለሌሎች እንዲያሳውቁ የሚረዳ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሥልጠናውን የወሰዱት ከ130 በላይ ተመራቂዎች የአዲስ አበባ፣ የአድማስ፣ የጌጅ እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መኾናቸው ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!