በጎንደር ከተማ 61 መማሪያ ክፍሎችን እንደሚገነባ የአማራ ልማት ማኅበር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

14

ጎንደር: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 በጀት ዓመት በጎንደር ከተማ በአማራ ልማት ማኅበር እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ 61 መማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት እቅድ መያዙን የጎንደር ከተማ የአማራ ልማት ማኅበር ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በትምህርት ቤቶች እያጋጠሙ ያሉ እና የሚያጋጥሙ የግብዓት እጥረቶችን ለመፍታት ያለመ ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

ከተማ አሥተዳደሩ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ሥራ እቅዱን ለባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅ ንቅናቄም ጀምሯል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ነፃነት መንግሥቴ የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ በትምህርት ቤቶች እያጋጠሙ ያሉ እና የሚያጋጥሙ የግብዓት እጥረቶችን በተባበረ ክንድ ለመፍታት ያለመ ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመኾን እና ረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጡ መማሪያ ክፍሎች የመፍረስ አደጋ የተጋረጠባቸው መኾናቸው በትምሕርት ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲፈጥር መቆየቱንም አንስተዋል። ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ኾነው እንዲቆዩም አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

ከ2014 ዓ.ም በፊት 96 በመቶ የሚኾኑት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች እንደነበሩ ያስታወሱት ምክትል መምሪያ ኀላፊው አሁን ላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ 19 በመቶ ማሻሻል ተችሏል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 135 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር መታቀዱንም ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ የአማራ ልማት ማኅበር ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደባባይ ሙሉጌታ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ያለውን የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ለመቅረፍ ምቹ የመማሪያ ክፍሎች ገንብቶ የማስረከብ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብቻ በአልማ እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ 61 መማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት እቅድ ተይዟልም ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ
ባለፈው ዓመት ለ2 ሺህ 900 ተማሪዎች በ11 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መጀመሩን አንስተዋል። በ2017 የትምህርት ዘመን ሁሉንም ክፍለ ከተሞች በማስተባበር ምገባው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ንግድ እና ገቢያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ትውልድ ለመገንባት መምህራን፣ ወላጆች፣ የሥራ ኀላፊዎች እና ዲያስፖራው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ምቹ የመማሪያ ስፍራዎችን መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው ተገለጸ።
Next articleከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።