
👉 ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል።
ከሚሴ፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ በ2016 በጀት ዓመት የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለምረቃ በቅተዋል።
የከሚሴ ከተማ ከተማ እና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሁሴን የሱፍ በ2016 በጀት ዓመት ከ18 በላይ ፕሮጀክቶች ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ በውስጥ ገቢ እና በክልሉ መንግሥት ድጋፍ የተገነቡ መኾናቸውን ገልጸው ለኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
በቀጣይ የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በመለየት ምላሽ ለመስጠትም በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በ2016 በጀት ዓመት በውስጥ ገቢ፣ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ከ90 በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይ በየአካባቢው ያለውን የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች በመለየት ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሠራል ነው ያሉት።
አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም በማሸጋገር የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ፕሮጀክቶቹ በአካባቢያቸው በመገንባታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።
በከተማው ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ውስጥ የኮብልስቶን መንገዶች፣ ሼዶች፣ የወጣቶች መዝናኛ፣ የውኃ ማፋሰሻ፣ መንገዶች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም ይገኙበታል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!