
ሰቆጣ: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ከዩኒሴፍ ኢዩ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ እና የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ያለመ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጤና መምሪያ እና የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ መሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አፈጻጸም እና የ2017 ዓ.ም የዕቅድ ትውውቅ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይም በየዓመቱ የሚከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል መደረግ ስለሚገቡ ተግባራት ከጤና ባለሙያዎች ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድም ነው የተብራራው።
የንቅናቄ መድረኩ ከነሐሴ 11/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይም ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!