የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ከማኅበረሰቡ ጋር በትብብር እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

29

ሰቆጣ: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጻግቭጂ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሐመልማል ጥበቡ አሁን ያለው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ከመንግሥት ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌላው የጻግቭጂ ወረዳ የጻታ ከተማ ነዋሪው ወጣት ተስፋየ ደባሽ ሰላም እንዲሰፍን ከሌሎች ወጣቶች ጋር እየሠራ መኾኑን እና በተግባርም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጸው።

የክልሉ መንግሥት ለሰላም ባደረገው ጥረት በጻግቭጂ ወረዳ ሰላምን ማረጋገጥ መቻሉን የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኽሉፍ ሰሎሞን አስገንዝበዋል።

ሁሉም ቀበሌዎች የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከሰላም ወዳዱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

በዋግ ኽምራ ያለው ሰላም አበረታች መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌታወይ አብርሃ ተናግረዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች በጋራ የሠሩት ሥራ አካባቢው ላይ ሰላም እንዲረጋገጥ ማገዙንም ነው ያብራሩት፡፡

ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም በሰቆጣ ከተማ የሚከበረው የልጃገረዶች የሻደይ በዓል በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ።
Next articleበሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የእናቶችን እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ያለመ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።