24 በርሚል ቤንዚን በሕገወጥ መንገድ ሲቀዳ መያዙን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

27

ወልድያ፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወንድሙ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 2:00 ሰዓት አካባቢ ወልድያ ከተማ ደብረገሊላ የሚገኘው ነዳጅ ማድያ ላይ 24 በርሚል ወይም በሊትር 2 ሺህ 480 ሊትር ቤንዚን ሲቀዳ እጅ ከፍንጅ መያዙን ነው የገለጹት።

መምሪያ ኀላፊው የነዳጅ ችርቻሮ የሚፈቀድላቸው ወረዳዎች ከከተማ አሥተዳደሩ የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር ትስስር ያላቸው መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡

የተያዘው የነዳጅ ጭነት ከመምሪያው ጋር ትስስር ያልፈጠረ እና ያልተፈቀደለት ነው ብለዋል።

ነዳጅ ሲቀዱ የነበሩት ሠራተኞች ማምለጣቸውን የገለጹት መምሪያ ኀላፊው ነዳጅ ሲጭን የነበረው ታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 B59925 አዲስ አበባ የኾነ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር እንደዋለም ነው ያብራሩት።

በከተማ አሥተዳደሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንደ ሰበብ በማድረግ የዋጋ ንረት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን የመቆጣጠሩ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስገንዝበዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ተከዝኖ የተደበቀን ከ700 ኩንታል በላይ ሽንኩርት ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም መያዙንም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

የንግድ ቁጥጥሩን ለማሳለጥ የኅብረተሰቡ ጥቆማ የላቀ ሚና ነበረው ያሉት አቶ አዲሱ ፤ ሕዝቡ ሕገወጦችን በመጠቆም ወደፊትም እንዲተባበር አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት ለፍጆታ የሚውሉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለተጠቃሚው መቅረቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡
Next articleየድሬዳዋ አሥተዳደር የምክክር ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ አስረከቡ።