በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት ለፍጆታ የሚውሉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለተጠቃሚው መቅረቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡

39

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ እንዳልካቸው ሲሳይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ272 ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም 169 ሺህ 600 ኩንታል ምርቶችን በትስስር ለማቅረብ ታቅዶ በተደረገው ጥረት 190 ሺህ 167 ኩንታል ምርት እና 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ከዕቅድ በላይ መከናወኑን አመልክተዋል።

ይህም ጤፍ በገበያ ከሚሸጥበት ዋጋ በኩንታል ከ400 ብር እስከ 2 ሺህ ብር፣ ማሽላ ከ100 እስከ 600 ብር፣ በቆሎ እስከ 300 ብር ቅናሽ በማድረግ ለተጠቃሚው እንዲቀርብ የተደረገውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለግብይቱ እንቅስቃሴም 346 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት መሥራቱን ገልጸው የዳቦ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ስኳር፣ ዘይት እና ሌሎች ምርቶች ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ በትስስር በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ የተጣለባቸውን ኀላፊነት እየተወጡ መኾኑን አስታውቀዋል።

ባሕር ዳር የሚገኘው የመርከብ ዩኒየን የግብይት ክፍል ኀላፊ እንዳለው ታፈረ ዩኒየኑ ገበያው እንዲረጋጋ 1ሺህ 200 ኩንታል የጤፍ ምርት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም ለመንግሥት ሠራተኞች ከ2 እስከ 4 ወር ተከፍሎ የሚያልቅ በኩንታል ከገበያ ዋጋ እስከ 1ሺህ 500 ብር ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ መኾናቸውን አመልክተዋል።

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ መኳንንት ካሳሁን ከዩኒየኑ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ያለው የምግብ እህል የኑሮ ጫናው እንዲቃለል እያገዘ ነው ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን በ2017 በጀት ዓመትም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በትስስር ለተጠቃሚው እንዲቀርብ የማመቻቸቱ ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመላው ኢትዮጵያ የሲስተም ማሻሻያ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገለጸ።
Next article24 በርሚል ቤንዚን በሕገወጥ መንገድ ሲቀዳ መያዙን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።