“የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመኾን አካባቢውን ለመጠበቅ እና ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው” የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ

107

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ክልሉ አንድ ዓመት በሞላው የሰላም እጦት ውስጥ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ እስካሁን ድረስ የሰላም መደፍረስ ችግር አጋጥሞት መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡

የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት በርካታ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ሰላማዊ ውይይቶች ሲተገብር መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡

ጥያቄ እና ሃሳብ አለኝ የሚል እንዲቀርብ እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥረት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ የሰላም ጥረቱን ወደጎን የገፉ የታጠቁ ኃይሎች በክልሉ ቀውስ መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በፈጠሩት ቀውስ የሰው ሕይዎት ጠፍቷል፣ ሃብት እና ንብረት ወድሟል፣ ማኅበራዊ እንቅሰቃሴች ተመሰቃቅለዋል፣ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ተወዳደሪ እንዳንኾን አድርጓል፣ ለክልሉ የማይመጥን ሁኔታዎችን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

የክልሉን የጸጥታ ኃይል መልሶ በማደራጀት እና በማሠልጠን የጸጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎች ወደ ሰላም ለመመለስ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል፡፡ አካባቢዎችን ከታጠቁ ኃይሎች ነጻ ከማድረግ ጎን ለጎን የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን የመፍታት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ የታጠቁ ኃይሎች ከተሞችን ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ እያደረጉ መኾቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ከተሞች ላይ በማፈንዳት፣ ንጹሕንን በመግደል፣ በማገት ኅብረተሰቡ ከገባባት ቀውስ እንዳይወጣ ተዳጋጋሚ ችግሮችን እየፈጠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች ክብር እንደማይሰጡም ገልጸዋል፡፡

ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ከእኩለ ቀን በኋላ በተነዛው ሃሰተኛ መረጃ በባሕር ዳር ከተማ ሱቆች እንዲዘጉ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ማኀበረሰቡ ሃሰተኛ መረጃዎችን እየተቀበለ መሸበር እና ሥራውን ማቆም እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ከተማ ዝም ተብሎ የሚገባበት አይደለም ብለዋል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ፍንዳታ የፈጸሙ አካላት የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ ሌሎችንም ለመያዝ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ሃሰተኛ መረጃዎችን እየሰማ ሱቆችን መዝጋት፣ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረግ ማቆም እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ አካባቢው እንዲተራመስ የሚነዛውን ሃሰተኛ ወሬ ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት ጋር በመቆም ሰላሙን ለማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሚዘርፍ፣ ምጣኔ ሃብትን የሚያደቅ፣ የሕክምና እና የትምህርት አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚያደርግ፣ ሕይዎትን የሚያወሳስብ ቡድን ለሕዝብ ጠላት እንጂ ወዳጅ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ማኀበረሰቡ ተው በማለት መገሰጽ እና ሰላሙን ማስጠበቅ ይገበዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመኾን አካባቢውን ለመጠበቅ እና ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው ነው ያሉት፡፡ ወደ ሰላም አማራጭ የሚመጣ ካለ መምጣት ይችላል፤ ከዚህ ውጭ የኾነ አካሄድ ካለ ግን እርምጃ ለመውሰድ እና ለማስተካከል የሚያስችል ብቁ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት፡፡

ማኀበረሰቡ ወደ ኋላ የሚመለስ፣ አውዳሚ አስተሳሰብ መቃወም እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡ የታጠቁ ኃይሎች ለሃሰተኛ መረጃ ማሰራጫነት የሚገለገሉባቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የተዘረጉ ሃሰተኛ ሚዲያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው በሃሰተኛ ማሠራጫዎቹ አማካኝነት ባሕር ዳርን ተቆጣጠርን እያለ እያስወራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በተደጋጋሚ ስለ ባሕር ዳር ሃሰተኛ መረጃዎች ተሰራጭተዋል፣ ባሕርዳር ላይ የተፈጠረ ምንም ነገር የለም፣ ኅብረሰተቡ በሃሰተኛ መረጃ ተደናግሮ ሱቅ መዝጋት፣ ሥራውን ማቆም አይገባው ነው ያሉት፡፡

ከተማ ዘው ብሎ መቆጣጠር የሚያስችል አቅምም ብቃትም የለውም፣ የጸጥታ ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጓል፣ ይሄን ማረጋገጥ አፈልጋለሁ ነው ያሉት፡፡

የታጠቁ ኃይሎች አካሄድ ለሀገር የማይጠቅም፣ ሀገርን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ በኋላ በቃን ልጆቻችን ልታስጨርሱ ነው፣ ግጭቱ ተገቢ አይደለም፣ ሕይዎታችንን እያወሳሰበ ነው በማለት እየተቃወመ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሰላም ወዳድ ነው፣ ለሰላሙ መከበር ከመንግሥት ጋር የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ በሃሰተኛ መረጃ መረበሽ እና ሥራን ማቆም፣ ፈጽሞ ሊኾን አይገባም፣ መስተካከል አለበት ነው ያሉት፡፡

መንግሥት ለሰላም ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኝት በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ የታጠቀው ኃይል ራሱን ለውይይት አዘጋጅቶ እስከ መጣ ድረስ በራችን ክፍት ነው፣ በኃይል ለመጣ ግን እርምጃ ለመውሰድ ብቁ ዝግጅትም፣ ብቃቱም አለን ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎቻችን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና በሚል የጀመርነውን ራዕያችንን በሚያሳካ መንገድ እየተተገበሩ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next article“በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የተፈጠረ የጸጥታ ችግር የለም” የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን