
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የስርዓተ ምግብ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን፣ የልማት ቱሩፋት እና የነፃ ንግድ ቀጣና ሥራዎችን በድሬዳዋ ከተማ ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልጸዋል። ሥራዎቹ የተሳሰረ የልማት ፓኬጅ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ የኾኑ ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ራሳቸውን መቻላቸውን እንዲሁም ልጆቻቸውም የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ እንደኾነ አይተናል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት የተጀመሩ ሥራዎችም የሚበረታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በከተማ ግብርና እና የሌማት ቱሩፋትም በቂ የወተት፣ የእንቁላል እና የማር ውጤቶችን በማምረት የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል እና ገበያውን የሚያረጋጉ ሥራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላው በጉብኝታቸው የተመለከቱት የነፃ ንግድ ቀጣና ነው። ይህም በማምረቻ ኢንዱስትሪ እንዲሁም በገቢና ወጭ ንግድ ማዕከል ለመኾን የሚያስችል ሲኾን ለኤክስፖርት ብቻ ሳይኾን ተኪ ምርት ላይም ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት “በአጠቃላይ የተመለከትናቸው ሥራዎች በተናበበ እና በተሳሰረ መልኩ በትጋት ከሠራን የበለፀገ ሀገር እና ማኅበረሰብ በመፍጠር ምሳሌ የመኾን ጉዟችን በአጭር ጊዜ ይሳካል” ሲሉ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
