“ጭር ሲል አልወድም ለማን ይበጃል?”

43

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም ፀጥታ ቢሮ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ለብዙኅን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል። የመግለጫው ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ሰሞኑን በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው የአመፅ ጥሪ እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።

መንግሥት እና ሕዝብ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት እና ግጭት በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ እራሱን የጎጃም ፋኖ በሚል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከነሐሴ 07 እስከ 12/2016 ዓ.ም የተሽከርካሪ ማቆም አድማ እና ከነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ከቀኑ 7 ስዓት ጀምሮ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ገብተን ጦርነት የምንጀምር በመኾኑ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲቆም በሚል የተላለፈውን ተራ የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት መነሻ በማድረግ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ በመደረጉ የክልሉን መንግሥት እና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ አሳዝኗል።

የከተማችንን ሕዝብ በውሸት እና በአሉቧልታ ወሬ ላይ ተመስርቶ ሽብር በመፍጠር ሰላሙን ለመንጠቅ እና የዕለት ከዕለት የኑሮ መስተጋብሩን በመረበሽ ጫካ ላይ የለመደውን ዝርፊያ እና ቅሚያ ከተማ ውስጥ ጎትቶ ለማስገባት ያደረገውን ሙከራ ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ጋር ተቀናጅቶ መመከት እና አሉባልታውን ማክሸፍ ሲገባው “ጭር ሲል አልወድም” በሚል የዝርፊያ እና የቅሚያ ፊሽካ ተንበርካኪ በመኾን የሥራ እንቅስቃሴ መቆሙ በከፊልም ቢኾን የታየው ድርጊት አሳዛኝ ነው።

ይህ ታጣቂ ቡድን ላለፉት ቀናትም ሰላማዊቷን ባሕር ዳር ከተማን ለመረበሽ እና ጨለማ ውስጥ ለመክተት ብሎም ሕዝቡን በኑሮ ውድነት ለማሰቃየት በማሰብ ለመንገድ መስሪያ የመጣን ድማሚት ፈንጅ በከተማው ውስጥ የተለያዩ ሰላማዊ ዜጎች በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ተደጋጋሚ ፍንዳታ በመፍጠር ሕዝቡን ለመረበሽ ጥረት እያደረገ ነው።

ከሰላም ወዳዱ የከተማችን ሕዝብ ጋር በትብብር በመኾን ይህንን ህልም ለማክሸፍ እየተሠራም ይገኛል። በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው ፈንጅ የሚያፈነዱ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

አሁንም ቢኾን የክልል እና የፌደራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅር በቅንጅት እና በፍፁም ሕዝባዊነት ቆመው ሕግ እያስከበሩ በመኾናቸው ሕዝባችን ከእንደዚህ ዓይነት የማኅበራዊ ሚዲያ የአሉባልታ፣ የሽብር መልዕክቶች እና ቅስቀሳዎች ራሱን ጠብቆ የነበረውን ማኅበራዊ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል እና መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የሰላሙ ባለቤት በመኾን ከመንግሥት የፀጥታ አባላት ጎን በመቆም አጋዢ እና ተባባሪ እንዲኾን ጥሪ እናቀርባለን።

ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በከተማው ውስጥ ትጥቅ ይዞ በተለየ ሁኔታ የኃይል እንቅስቃሴ በሚያደርግ አካል ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ርምጃ የሚወስድ መኾኑን እናሳውቃለን።

“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም”

ከአብክመ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም
ባህር ዳር!!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ልንሠራ ይገባል” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ
Next article“ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎቻችን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና በሚል የጀመርነውን ራዕያችንን በሚያሳካ መንገድ እየተተገበሩ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ