“የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እየሠራን ሰላምን ማስጠበቅም አንዱ ተግባር መኾን አለበት” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

22

ጎንደር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2016 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር የአፈጻጸም እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድን ገምግሟል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመት የሰላም ችግሩን ከመፍታት ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የተሠሩበት መኾኑን ጠቁመዋል።

በከተማዋ በበጀት ዓመቱ ማገባደጃ ላይ የተጀመሩ የአብያተ መንግሥታት ጥገና እና የኮሪደር ልማቶች ለቀጣዩ ዕቅድ መነሻ እንደሚኾኑ አንስተዋል፡፡

“የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እየሠራን ሰላምን ማስጠበቅም አንዱ ተግባር መኾን አለበት” ብለዋል።

በመድረኩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2017 ዕቅድ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በ2016 በጀት ዓመት እንደ ከተማ ምንም እንኳን የሰላም እጦት ቢኖርም የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መሠራታቸውን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት መሪዎች ቁርጠኛ መኾን እንዳለባቸውም ምክትል ከንቲባዋ አሳስበዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ዮናስ ይትባረክ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት እንዲከበሩ መደረጉን አንስተዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ታዘባቸው ነጋ የከተማዋን መሠረተ ልማት በማልማት ምቹ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመፍታት ጥረቶች መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የኮብል ስቶን ሥራ እና የድልድይ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ሥራዎች መሥራታቸውን ገልጸዋል።

ከ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በመነሳት በ2017 በጀት ዓመትም ከክልል ተጀምሮ እስከ ከተማ እየወረደ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም በትጋት እንደሚሠሩም መሪዎቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፀጥታ መዋቅሩ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ስለሚገኝ ባሕር ዳር ላይ የሚፈጠር ነገር አይኖርም” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next article“ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ልንሠራ ይገባል” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ