
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 02/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‘‘ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ’’ 700 ሺህ ብር የሚሆኑ የምግብ እና ንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶችን ድጋፍ አደረገ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ (ኮካ ኮላ) ግምታቸው 700 ሺህ ብር የሚሆኑ ምግብ እና የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ፓስታ፣ ማኮሮኒ፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይት እና የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡
በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ የባሕር ዳር ፋብሪካ ምርት ክፍል ኃላፊ ኤባ መላኩ እንደገለጹት የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ተደርጎ በኩባንያው ተመርቶ ነው የቀረበው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግበረ ኃይል የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ዓለሙ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል ሀብት መሰብሰብ ከተጀመረበት ጀምሮ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ ተሰብስቧል፡፡ የተሰበሰበው ሀብት ከተወሰኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ብቻ እንደሆነ ገልጸው፤ በመሆኑም ችግሩን ለማለፍ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ