“ቶሎ ሕክምና በማግኘቴ ተረፍኩ”

29

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እድሜያቸው በ50ዎቹ መጨረሻ አካባቢ እንደኾኑ የሚናገሩት አዛውንት የሚኖሩት ባሕርዳር ወራሚት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።

እኝህ አባት በትምህርት ብዙም እንዳልገፉ እና በዱካ (በጣታቸው) እንደሚፈርሙ ይገልጻሉ። ገራገር፣ ቅን እና ለሰዎች አዛኝ እንደኾኑ ከንግግራቸው መገንዘብ ይቻላል።

አዛውንቱ ከሰሞኑ በጠና ታመው አዲስ ዓለም/ባሕር ዳር / ተብሎ በሚጠራው ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው ስለመኾኑ ነገሩን።

አሚኮ ምህረቱን እንዲሰጣቸው ከተመኘ በኋላ ለመኾኑ በምን አጋጣሚ እና ኹኔታ ወደ ሆስፒታሉ ሊመጡ እንደቻሉ እንዲገልጹ ጠየቃቸው።

ገራገር የኾኑት እኝህ አባት ቤተሰብ ለማሥተዳደር በአናጺነት ሙያ ይተዳደሩ እንደነበር ገልጸዋል። በዚሁ ሳምንት ቤት ለመጠገን ተስማምተው ብዙም ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ወደሚገኝ ሰው ቤት ሂደው ሥራቸውን ሲከውኑ ውለው የቀረበላቸውን ምሳ እና የሚጠጣውን መቀማመሳቸውን ነግረውናል።

አዛውንቱ ምግቡን እና የሚጠጣውን ከወሰዱ በኋላ ግን ወደ ምሽት አካባቢ የተፈጠረውን ለመናገር እጅግ ይከብዳል ይላሉ።

በፍጥነት ወደ መጸዳጃ ቤት ያመላልሳቸው እንደነበር ገልጸው በዚህም ምክንያት ራሳቸውን መቋቋም ሲያቅታቸው ወደ ሕክምና ማምራታቸውን ገልጸዋል።

በተደረገላቸው ሕክምናም የኮሌራ በሽታ መኾኑ በመረጋገጡ በአዲስ ዓለም ሆስፒታል ለይቶ ማከሚያ እንደገቡ እና በተደረገላቸው እገዛ አሁን ላይ እያገገሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“እድለኛ ኾኘ ቶሎ ሕክምና በማግኘቴ ተረፍኩ እንጅ ትንሽ ብቆይ አሁን ይህን ሁኔታ ባልገለጽኩ ነበር” ሲሉ ስለኹኔታው አስከፊነት ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሰፊ ደርብ ኮሌራ በክልሉ በ2015 ዓ.ም በ16 ዞኖች እና በ58 ወረዳዎች በመከሰቱ 5 ሺህ ያህል ሰዎችን አጥቅቶ 90 ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉን አስታውሰዋል።

በወቅቱም መንግሥት፣ አጋር አካላት እና ኀብረተሰቡ ባደረጉት ርብርብም በሽታውን መቆጣጠር መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በሽታው አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ?

በዚህ ዓመትም በሽታው በድጋሚ ተከስቶ ሰዎችን እየጎዳ ስለመኾኑ አብራርተዋል። በሽታው ሰፋፊ የእርሻ አካባቢ ባለባቸው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፣ በጎንደር ከተማ እና በዙሪያ ወረዳው፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ በባሕር ዳር ከተማ እና በዙሪያ ወረዳው በስፋት እየተሰራጨ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት።

በርካታ ኀብረተሰብም በበሽታው ተጠቅቷል ብለዋል። እስከ ታኅሣሥ/2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ 4 ሺህ 983 ሰዎች በበሽታው እንደተጠቁ አስረድተዋል፡፡

ባለሙያዋ በያዝነው ሳምንት ብቻ እንኳን 292 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡ የሰላም ኹኔታውም በሽታውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በችግርም ውስጥ ተኾኖ ችግሩን ለመቆጣጠር እና ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ በልዩ ኹኔታ ክትትል የሚደረግባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አስገንዝበዋል፡፡

በሽታው መቸ ይከሰታል?

“በተለይ ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና የመጸዳጃ ቤቶች በሌሉባቸው ሥፍራዎች፣ በሰፋፊ የእርሻ አካባቢዎች እና ኀብረተሰቡ ተፋፍጎ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ወረርሽኙ በፍጥነት በመስፋፋቱ ሰዎችን እያጠቃ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ድርቅ በተከሰተባቸው 43 ወረዳዎችም በሽታው በስፋት መከሰቱን ነው ያብራሩት፡፡

በሽታውን እንዴት እንከላከል?

በሽታውን ኀብረተሰቡ ውኃን አክሞ ወይም አፍልቶ በመጠጣት፣ በመጸዳጃ ቤት በአግባቡ በመጠቀም፣ ምግብን አብስሎ በመመገብ እና የግል ንጽህናን በመጠበቅ በተለይ ደግሞ እጅን በሳሙና በመታጠብ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚችል ነው የተናገሩት።
የኮሌራ በሽታ የት እና እንዴት ይታከማል?

የኮሌራን ክትባት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎቱ በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም ሁሉ ስለሚሰጥ ሕክምናውን በአግባቡ በመውሰድ በሽታውን መግታት እና መቆጣጠር እንደሚቻልም ነው የተብራራው።

የኮሌራ በሽታ ካልታከመ ምን ይከሰታል?

አንድ በኮሌራ በሽታ የተጠቃ ሰው ካልታከመ በአምስት ቀናት ውስጥ ሕይዎቱን ሊያጣ እንደሚችል የገለጹት ባለሙያዋ በቀላሉም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ በመዛመት በፍጥነት ገዳይ በሽታ ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወላጆች ከነሐሴ 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ማስመዝገብ አለባቸው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ
Next articleየተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን በማስቀጠል በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።