
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ከነሐሴ 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ ትምህርት መምሪያ ገልጿል።
መምሪያው የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አፈፃፀም እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ላይም ከሚመለከታቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በደብረ ማርቆስ ውይይት አካሂዷል።
በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት የዘለቀው የሰላም እጦት በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ የጎላ ነበር፡፡
በክልሉ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደርም 17 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደነበሩ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ ለአሚኮ ተናግረዋል።
የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተሟላ መልኩ እንዲከናወን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ኀላፊው ሁሉም ወላጅ ከነሐሴ 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ማስመዝገብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ በ2016 የትምህርት ዘመን የነበሩ ችግሮች በ2017 የትምህርት ዘመን እንዳይቀጥሉ በማድረግ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በርካታ ተማሪዎች ቤት በመዋላቸው የሥነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎችም ለሀገር ዕድገት መሠረት የኾነውን የትምህርት ሥርዓቱን ለመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ የመማር መስተማር ሥራውን በተሳካ መንገድ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!