
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት እንደገለጹት መንግሥት ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአማራ ክልል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በዕለቱም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ጽድ፣ ግራር፣ ባሕር ዛፍ፣ ግራቢሊያ፣ ዲከረስ እና መሰል ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያን ጨምሮ ሌሎች የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅሰው”ለተከላ የተዘጋጁ አብዛኞቹ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞች ወደ መትከያ ቦታዎች እንዲጓጓዙ ተደርጓል” ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በዕለቱ በነቂስ ወጥቶ የችግኝ ተከላውን እንዲያከናውን የቅስቀሳ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው የመትከያ ስፍራ ካርታን መሠረት ተደርጎ ለሚተከለው ችግኝ ኅብረተሰቡ ተገቢ እንክብካቤ እና ጥበቃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በቴክኖሎጅ ታግዘው ከተከላ ቦታዎች ወደ ማዕከል መረጃ የሚያደርሱ ባለሙያዎችም ተገቢ ዝግጅት አድርገው የተከላ ቀኑን እየተጠባበቁ መኾኑን አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እንየው ዓለሙ እንደሚሉት በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ ከወዲሁ ዝግጅት አድርገዋል።
ችግኝን መትከል ብቻ ሳይኾን የተከሉትን ተንከባክበው የማሳደግ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።
በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታረቀኝ ካሳሁን በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከመሳተፍ ባለፈ የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክበው ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በክልሉ በዘንድሮው የክረምት ወራት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለመትከል ከተዘጋጀው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስካሁን 88 በመቶ ተተክሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!