
ደሴ: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ”ትምህርት ለትውልድ” የንቅናቄ መድረክን ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በ2016 የትምህርት ዘመን የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት የተደረገው ጥረት መልካም እንደነበር አንስተዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ በጀት በመመደብ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ያስጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምም የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ አዎንታዊ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
ይህን ማስቀጠል እና ወላጆች የልጆቻቸውን ውጤት መከታተል ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ በከተማዋ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ለማድረግ እና አቋራጭ ተማሪዎችን ለመቀነስ የተሠራው ሥራ ውጤት ማምጣቱን የገለጹት ኀላፊው ለ2017 የትምህርት ዘመንም ከ42 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል።
የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን በማስቀጠል በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ነው አቶ መንግሥቱ ያስታወቁት።
ለዚህም ከተማ አሥተዳደሩ ከሚይዘው በጀት ባሻገር ባለሃብቶች እና አጋር አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ምክክር እየተደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!