“ምንዳውም እዳው በእጃችን ነው፤ እዳውን የመቀነስ ምንዳውን የመጨመር ታሪካዊ ኀላፊነት ተጥሎብናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

35

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ደረጃ የሚካሄደውን የ2016 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅን አስጀምረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የ2016 ክልላዊ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ ተካሂዷል፡፡ እሱን ተከትሎም በሁሉም ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የ2016 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ ተጀምሯል፡፡

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልእክት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በእውነት፣ በቅንነት እና በመርሕ ላይ ተመሥርቶ መገምግም ለ2017 እቅድ ትግበራ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያግዛል ብለዋል፡፡

“ክልሉ ላለፈው አንድ ዓመት የቆየበት ነባራዊ ሁኔታ ግልጽ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ሥራዎች ዙሪያ እውነት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

በክልሉ የነበረው የሰላም እጦት በምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ዙሪያ መለስ ግምገማ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ካለፈው ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና ውይይት በኋላ በመጪው ዓመት እቅድ ላይ በሚገባ ተነጋግሮ የጋራ መግባባት መያዝ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ በመልእክታቸው እቅዱ የክልሉን ነባራዊ ኹኔታ በውል የሚለውጥ በመኾኑ በባለቤትነት መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በእቅዱ የተቀመጡ ግቦች እና ተግባራት ተፈጻሚ እንዲኾኑም በግል እና በጋራ ኀላፊነት መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በየደረጃው የተቀመጡት የእቅድ ግቦች እና ተግባራት ያለድካም እና ያለውጣ ውረድ የሚሳኩ አይደሉም ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ ለክልሉ ሕዝብ ሲባል ራስን ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ “በሕዝብ ወንበር ላይ ተቀምጦ የራስን ሕይዎት ብቻ መምራት በፍጥነት ሊቆም ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በየደረጃው ያለው መሪ የተቀበለው ኀላፊነት ወቅቱ የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል የሚያስገድድ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ምንዳውም እዳው በእጃችን ነው፤ እዳውን የመቀነስ ምንዳውን የመጨመር ታሪካዊ ኀላፊነት ተጥሎብናል” ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተለያየ ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በፅናት መታገል እና ማረም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ገለጹ።
Next articleበሰቆጣ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።