
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደጀን ከተማ ተካሂዷል።
ዞኑ በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን በደጀን ከተማ ገምግሟል።
ባለፈው ዓመት በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫናዎች መፈጠሩ ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ በማኅበረሰብ ጤና መድኅን አፈፃፀም፣ በግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት፣ በገቢ አሠባሠብ ሥርዓቱ ላይ በጫናም ውስጥ ኾኖ ውጤቶች መመዝገባቸው በግምገማ መድረኩ ተነስቷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ እንቅፋት ቢኾንም በየአካባቢያቸው ሕዝባቸውን በማስተባበር የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።
መሪዎቹ በ2017 በጀት ዓመት የተያዙ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኛ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በየደረጃው የሚገኙ የዞኑ ሕዝብ መሪዎች ከዚህ በፊት በተለያየ ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በፅናት መታገል እና ማረም በተያዘው በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ግቦች እንዲሳኩ ሕዝቡን በንቃት ማሳተፍ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ሕገ ወጥነትን መቆጣጠር እና የኑሮ ውድነትን ማርገብ በ2017 በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አስገንዝበዋል።
በደጀን ከተማ አሥተዳደር በተካሄደው የአፈፃፀም እና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ከዞኑ የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የዞን እና የወረዳ መሪዎች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!