ሼህ መሐመድ አላሙዲን ለኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ኅብረት ዕውቅና ሰጣቸው።

16

ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ኅብረት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር፣ በደቡብ አፍሪካ የ15 ቀናት ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ ቆይቷል።

በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደው ይኽ ጉባኤ በዘንድሮው ጉባኤው ላይ ከ3ሺህ 200 በላይ የምርምር ውጤቶች የቀረቡበት እና በርካታ የዓለም ባለሙያዎች በአካል እና በበይነ መረብ የተሳተፉበት ነው፡፡ ኅብረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና ተቋማት በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ዕውቅና ይሰጣል፡፡

በዚህ መሰረት በዘንድሮው ጉባዔ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምረው ለኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ እድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ የክበር አባል እንዲኾኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ኅብረቱ የክብር አባል እንዲኾኑ ዕውቅና የሰጣቸው፡፡

ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ የሥልጠና እና ምርምር ማዕከል ሲቋቋም ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲን ከፍተኛውን አበርክቶ አድርገዋል። ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ኅብረት በአውሮፓውያኑ 2018 ቪዬና በተካሄደው ጉባኤ በኢትዮጵያ ለህዋ ሳይንስ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ላባረከቱት አቶ ተፈራ ዋልዋ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል።

ዓለም አቀፉ አስተርኖሚካል ኅብረት በአውሮፓውያኑ 1919 የተመሰረተ ነው።

ዓለም አቀፍ ህዋ እና ጠፈር ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚወስን ከ85 ሀገራት በላይ እና ከ12 ሺህ በላይ ተመራማሪዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሳዑዲ አረቢያ የሥራ ገበያ ፍላጎት እንዳለ እና ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article“ነሐሴ 17/ 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)