ሂጅራ ባንክ የማኅበረሰቡን የፋይናንስ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።

42

አዲስ አበባ: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሂጅራ ባንክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የኾነውን በሀላል የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያለመ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።

ሂጅራ ባንክ የማኅበረሰቡን የፋይናንስ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሠራ መኾኑም ተገልጿል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አብዱሰላም ከማል እንዳሉት ባንኩ በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን ቢያገኝም የሀላል ፋይናንስ ሥርዓቱ በሚፈለገው ልክ አላደገም ብለዋል።

ለዚህም ዋነኛው ችግር የግንዛቤ ክፍተት መኾኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አንስተዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም አሥተሣሠብ ላይ መሥራት ወሳኝ መኾኑን ነው የገለጹት። የሂጅራ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዳዊት ቀሎ ባንኩ አማራጭ የባንክ ሥርዓትን በመዘርጋት በዘመኑ ቴክኖሎጂ ታግዞ የተሟላ አገልግሎትን እየሰጠ ነው ብለዋል።

የሀላል ፋይናንስ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አዲስ እንደመኾኑ ባንኩ ከ140 በላይ ለሚኾኑ ዑለማዎች እና ምሁራን በዓለም አቀፍ አሠልጣኞች ሥልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሀላል ፋይናንስ ሥርዓት አቅም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ዓላማውን ማጎልበት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው።

በውይይቱ ላይ የፌደራል እና የክልል መጅሊስ ፕሬዚዳንቶች፣ ዑለማዎች፣ የግል እና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አዲስ ድረ ገጽ አስተዋወቀ፡፡
Next articleበሳዑዲ አረቢያ የሥራ ገበያ ፍላጎት እንዳለ እና ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡