የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አዲስ ድረ ገጽ አስተዋወቀ፡፡

57

ባሕር ዳር: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እና ቱሪዝም ሥራዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አዲስ ድረ ገጽ አልምቶ አስተዋውቋል፡፡ አዲስ የተዋወቀው ድረገጽ (AmharaTourism.gov.e) የሚል ነው። አዲስ የተዋወቀው ድረ ገጽ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን፣ መዳረሻችን እና ታሪካዊ ክዋኔዎችን በቀላሉ ማግኘት እና ማስተዋወቅ እንደሚያስችላቸው ተመላክቷል፡፡

ድረ ገጹን ያለማው የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሸን ነው። የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን የሶፍትዌር ልማት ባለሙያ አበበ ጌትነት አዲስ የተዋወቀው ዌብሳይት የክልሉን የቱሪዝም መረጃ ለመያዝ እና ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ተናግሯል፡፡ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ድረገጹን ያበለጸገው አስተማማኝ መረጃ ለመያዝ እና ለመጠበቅ መኾኑንም ገልጿል፡፡ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባም አመላክቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለመኾን ድረገጽ ያስፈልጋል ነው ያለው። አዲስ የተዋወቀው ድረ ገጽም የክልሉን የባሕል እና የቱሪዝም መረጃዎችን በቀላሉ ማስተዋወቅ እንደሚያስችል ተናግሯል፡፡ አዲስ በተዋወቀው ድረ ገጽ ሊታዩ የሚገባቸው የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች እንደሚያሳይም ተመላክቷል። ስለ ተቋሙ እና ስለ መሪዎች መረጃ ይሰጣልም ተብሏል። በቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኙ ሆቴሎችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታነህ ባየ ኮሚሽኑ የክልሉን ተቋማት በቴክሎጂ ለማዘመን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መረጃዎች ተዓማኒ እና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የበለጸገው ድረ ገጽ ታማኝ የኾነ መረጃ ለሚፈለገው ማኅበረሰብ ማድረስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

ድረ ገጹን በአግባቡ ማስተዳደር፣ መረጃዎችን በፍጥነት መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ተቋማትን የማዘመን ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የተሻለ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የክልሉ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ድረ ገጹ ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መረጃ በመስጠት የክልሉን ሃብት እንደሚያስተዋውቅም ተናግረዋል።

በየዘመናቱ የተገኙትን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በአግባቡ መጠቀም ሀገራት በእድገት እንዲቀዳደሙ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡ ዘመናችን የመረጃ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ መጠቀም የምጣኔ ሃብት እድገትን እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡ የክልሉን ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡

አዲስ የተዋወቀው ድረ ገጽ የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎች በማስተዋወቅ የቱሪዝም ገበያው እንዲያድግ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ በቀላሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለመኾን እንደሚስችልም አመላክተዋል፡ ታሪክን መጠበቅ እና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በቱሪዝም ጸጋዎች ለመጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ ሰላም የቱሪዝም እስትንፋስ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ቱሪዝምን በጋራ መጠበቅ፣ በጋራ ማልማት፣ በጋራ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ሰላምን ማረጋገጥ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ጸጋ የበለጠ ማስተዋወቅ እና የቱሪዝም ገበያውን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያው ሰብሮ ለመግባት እና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ ዲጂታል ሚደያውን መጠቀም እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ የአመራር መዋቅሮች በጋራ ሊሠሩ ይገባል” የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መመሪያ ኅላፊ ፍቅር አበበ
Next articleሂጅራ ባንክ የማኅበረሰቡን የፋይናንስ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።