
ደሴ: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በ2016 የበጀት ዓመት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሢሰሩ መቆዬታቸውን አንስተዋል።
የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብርን በማስጀመር ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመገብ መቻሉ ተናግረዋል። ልዩ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መሠራቱም በጥንካሬ ተገልጿል። በከተማ አሥተዳደሩ የትምህርት ግብዓቶች እጥረት፣ የተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ማቋረጥ፣ የመምህራን የማስተማር ብቃት አለማደግ እና የትምህርት ጥራትን በተገቢው መልኩ መፈጸም አለመቻል በከተማ አሥተዳደሩ የታዩ ችግሮች እንደነበሩ በመድረኩ ተነስቷል። እነዚህን ችግሮች በተያዘው በጀት ዓመት ለመፍታት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ መጨመር ብሎም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የመመዝገቢያ ክፍያ መጨመር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸው በመድረኩ ተነስቷል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መመሪያ ኅላፊ ፍቅር አበበ “በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ የአመራር መዋቅሮች በጋራ ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የመምህራንን አቅም በተከታታይ ድጋፍ እና ሥልጠና ማዳበር እንደሚገባ እና የትምህርት አመራሩ እና የተማሪ ወላጆች በተሻለ ትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!