
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 የትምህርት ዘመን ትምህር ለመጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ማሻሻል አንዱ ተግባር ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጎርደማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገጽታ ማሻሻል ይገኝበታል። ትምህርት ቤቱ በእንጨት የተገነባ እና ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱ ለማስተማር እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር መስከረም አባተ ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት፣ ከአጋር አካላት እና ከማኅበረሰቡ በተገኘ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ስድስት ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መቀየር መቻሉን ገልጸዋል። ግንባታው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህር መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ እንደገለጹት በከተማ አሥተዳደሩ ከመንግሥት፣ ከአጋር አካላት እና ከማኅበረሰቡ በተገኘ 135 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለ2017 የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረግ ተችሏል።
ግንባታው 44 የመማሪያ ክፍሎች እና መጸዳጃ ቤቶችን፣ የአሥተዳደር ክፍሎችን፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የአሥተዳደር እና “አይቲ” ክፍሎችን እና የአጥር ግንባታ ሥራን ያካተተ ነው። የግንባታዎቹ 22 ነጥብ 5 በመቶ ወጭ በማኅበረሰቡ፣ 54 በመቶው ወጭ በአጋር አካላት፣ ቀሪው ወጭ ደግሞ በመንግሥት ተሳትፎ የተሸፈነ ነው።
የትምህርት ቤቶችን ግቢ በማስዋብ በኩል የማኅበረሰቡ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበርም ገልጸዋል። በቀጣይ ወራትም በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ እና አጋዥ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ከነሐሴ 20/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም የተማሪ ምዝገባን ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ከ120 ሺህ በላይ ተማሪዎችም ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!