በአማራ ክልል የተከሰተውን የወባ ሥርጭት መቀነስ ካልተቻለ በመስከረም እና ጥቅምት ወራት ላይ ከባድ የኾነ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቆመ።

10

ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል። ከሐምሌ ወር ጀምሮ በየሳምንቱ ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ እንደሚያዙም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በኢንስቲትዩት መስሪያ ቤቱ የወባ ኘሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንክር እንደተናገሩት አሁን ያለው የወባ ታማሚዎች ቁጥር ካለፈው ሰኔ ወር ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ የሚኾን ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

አቶ ዳምጤ አያይዘውም በደቡብ ጎንደር ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለው የወባ በሽታ ሥርጭት በክልሉ ከተከሰተው ዘጠና በመቶ የሚኾነውን ይሸፍናል ብለዋል፡፡

በኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስተባባሪነት የድንገተኛ ክስተት አሥተዳደር ማዕከል በማቋቋም ከዞን እና ከወረዳ በሚደርሱ መረጃዎች ክትትል በማድረግ የባለሙያ እገዛ እና የግብዓት ማሟላት ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳምጤ ችግሩን ለመቀነስ በ22 ወረዳዎች ለ233 ቀበሌዎች የኬሚካል ርጭት እየተደረገ እንደኾነ ገልጸዋል። ርጭት ውስጥ የማይካተቱ ጫና ያላባቸው ወረዳዎች ደግሞ የአጎበር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሥርጭቱን ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ካልተቻለ የወባ ዋና መተላለፊያ በሚባሉት መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ ከባድ የኾነ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሥሩ ወጣቶችን በወባ መከላከል እና መቆጣጠር ተግባር ላይ ተሳታፊ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። በተጨማሪም ውኃ ያቆሩ አካባቢዎችን ማፋሰስ እንዲሁም የግል እና አካባቢን ንፅህና መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አቶ ዳምጤ አያይዘዉም ኀብረተሰቡ የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ መጠቀም አለበት ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈ ማንኛውም ሰው የሕመም ስሜት ሲሰማዉ ፈጥኖ በአካባቢዉ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም ሄዶ በመመርመር የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሕግ ውጭ የትምህርት ክፍያ ጭማሪ አድርገው የነበሩ 26 ትምህርት ቤቶች ማስተካከያ ማድረጋቸውን የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ገለጸ።
Next articleበ132 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ ትምህርት ቤቶችን ለቀጣይ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረግ መቻሉን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ገለጸ።