“በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሠሩ የሚገኙት የመንገድ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ ናቸው” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ

17

ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በፈተናዎች ውስጥም ኾኖ የተለያዩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ በ2016 በጀት ዓመት በ63 ሚሊዮን ብር የአደባባይ እና የእግረኛ መንገድ ልማት እንዲሁም የተፋሰስ ጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑም ተመላክቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮዎችን በማምጣት በደብረ ማርቆስ ከተማ የተገነባው የመንገድ ዳር ልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ የእግረኛ መንገድ ልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ኀብረተሰቡ ላሳየው ቀና ትብበር ምሥጋናቸውን ያቀረቡት ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በ2017 በጀት ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በከተማዋ ከ1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል። በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የአደባባይ ልማትም ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁን እና በ2017 በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በጋራ እናክብር” የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ
Next article200 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል አገኙ፡፡