“ኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በጋራ እናክብር” የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ

32

ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በነሐሴ እና በጳጉሜን የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላቱ “ባሕላችን ለሰላማችን እና ለአንድነታችን” በሚል ሃሳብ ይከበራሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የድንቅ ታሪክ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት መኾኗንም ተናግረዋል። አንድነቷን እና ሰላሟን መጠበቅ ቢቻል ምጣኔ ሃብቷን ከፍ የሚያደርጉ የቱሪዝም ሃብት ያላት ሀገር መኾኗንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ደግሞ ሁሉንም የቱሪዝም ጸጋዎች የተጎናጸፈ ነው ብለዋል። ክልሉ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚገዙ ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ ሃብቶች፣ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን የያዘ መኾኑንም ነው የተናገሩት። ያልተነካ እና እምቅ የቱሪዝም ሃብት ያለው መኾኑንም አንስተዋል።

ከነሐሴ እስከ ጳጉሜን ድረስ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳ፣ እንግጫ ነቀላ፣ ቡሔ እና የሩፋኤል በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ አንስተዋል። ሻደይ በዋግኽምራ፣ ሶለል በሰሜን ወሎ ራያ፣ አሸንድዬ በሰሜን ወሎ እና በጎንደር ምሥራቃዊ ወረዳዎች፣ ቡሔ በደብረታቦር፣ ከሴ አጨዳ፣ እንግጫ ነቀላ እና ሩፋኤል በጎጃም በድምቀት እንደሚከበሩ ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊዉ የተናገሩት።

የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ወደ ክልሉ መጥተው በዓላቱን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል። ኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በጋራ እናክብር ነው ያሉት በመልዕክታቸው። በነሐሴ እና ጳጉሜን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ የሚከበሩ በዓላት የሕዝብ የማንነት መገለጫ፣ የኑሮ ዘይቤ ማሳያ ፣ የማኅበራዊ ትሥሥሩ መገለጫ፣ የትናንት እና የዛሬ ትውልድ መተሳሰሪያ እና ለነገው ትውልድ ልዩ ገጸ በረከቶች ናቸው ብለዋል።

በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ግብረ ኀይል አቋቁሞ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በዓላቱ ለዘመናት በሕዝብ ዘንድ እየተከበሩ የመጡ፣ የችግር እና የፍስሀ ዘመናትን ያሳለፉ የሕዝብ በዓላት መኾናቸውንም ገልጸዋል። በዓላት ሲከበሩ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መገለጫቸውን እንደያዙ መኾን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። በዓላቱ ሳይበረዙ፣ ሳይከለሱ፣ ድምቀታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

ቢሮው የክልሉን ባሕል፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ የመጠበቅ፣ የመንከባከብ፣ የሃብት ምንጭ የማድረግ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኀላፊነት አለበት ብለዋል። በዓላቱ በክልል ደረጃ ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም በባሕር ዳር እንደሚከበሩም ገልጸዋል። ክልላዊ በዓሉ ሲከበር ከባሕላዊ ክዋኔዎች ባለፈ ጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይት እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።

በበዓሉ የሚቀርቡ ክዋኔዎች ባሕላዊ ይዘቱን እና ማኅበራዊ እሴቱን የጠበቁ ብቻ እንዲኾኑ ይደረጋሉ ብለዋል። በዓላቱ የበለጠ እንዲተዋወቁ እና የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾኑ በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል። በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ጎብኝዎችን በመልካም እንግዳ አቀባበል በመቀበል፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ማሳየት እና የአካባቢ አምባሳደር መኾን ይገባልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ በ2016 በጀት ዓመት ከ41 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ተገንብቶ መጠናቀቁን ከተማ አሥተዳደሩ ገለጸ።
Next article“በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሠሩ የሚገኙት የመንገድ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ ናቸው” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ