
ባሕር ዳር: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ የሥራ አፈጻጸም እና የ2017 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ይገኛል። በመድረኩ የተገኙት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት ክልሉን ለማፍረስ የታሰበው አደጋ ተቀልብሶ መደበኛ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ከተማ አሥተዳደሩ ሰላሙን ከሕዝብ እና ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በማስጠበቅ ብሎም ቀን ከሌት ተግቶ በመሥራት የተጀመረውን 22 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በአብዛኛው ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል። አቶ ጎሹ አክለውም በቀጣይ ወደ አስፋልት እና የጌጠኛ ድንጋይ ሊያድግ የሚችል 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ 15 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድንም ማጠናቀቅ መቻሉን ነው አቶ ጎሹ የተናገሩት። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጨምረው እንደገለጹት በከተማዋ እየተከናዎኑ ያሉት የልማት ሥራዎች የኢኮኖሚ ችግሮችን የሚፈቱ፣ ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጡ፣ ባሕር ዳርን ጹዱ፣ ውብ፣ ማራኪ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። የዚህ አንዱ አካል የኾነው “የስማርት ባሕር ዳር ፕሮጀክት” በምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!