
አዲስ አበባ: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ሁነት ከአልሸባብ ጋር ተያይዞ ቢከሰት አትታገስም ብሏል መሥሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት መግለጫ በተርኪየ አንካራ ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ሁለተኛ ዙር ድርድር ተጠናቅቋል።
ድርድሩ በዋናነት ከመጀመሪያው ዙር ይልቅ የተሻለ የሚባል ለውጥ የመጣበት ነው። ለቀጣይ ዙር ድርድር ጥሩ መደላድል የተፈጠረበት ስለመኾኑም ነው ያብራሩት። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ስታነሳ አንደ ነውር ይታይ ነበር፤ አሁን ግን አደራዳሪውን የተርኪየ መንግሥት ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል የሚል ዕምነት ስለማሳደራቸው ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስለመደረሱ ማሳያ መኾኑን ነው የጠቀሱት። ከሶማሌላንድ መንግሥትም ይሁን ከሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር የሚደረገው ድርድር ይህንን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል። አሁን ላይ የአትሚስ ተልዕኮ መጠናቀቁን ተከትሎ እና የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግሥት የታሰበውን ኀላፊነት መሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ መኾኑ ከግንዛቤ ገብቶ አዲስ ተልዕኮ ለመስጠት እየተመከረበት ነው ብለዋል።
ይህም በዋናነት ከዚህ በፊት ልምድ ያላቸውን ሀገራት ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል። ግብጽ እና ጅቡቲም ለመሳተፍ ያቀረቡት ጥያቄ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት በመልካም ሁኔታ የተመለከተው ቢኾንም ውሳኔ ግን አላሳለፈም ነው ያሉት። በተለይ አልሸባብ የባሕር ላይ ዝርፊያ የሚያከናውን ቡድን ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በዚህ ምክንያት የዓለማችን ሃብታሙ አሸባሪ ቡድን አድርጎታል ብለዋል።
ድሮን ስለመታጠቁም መረጃ እንዳለ ነው ያስገነዘቡት። ስለኾነም ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አንደሚጋራ ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታት በመኾኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ታደርጋለች ነው ያሉት፡፡ ከሚለከታቸው ሀገራት እና ተቋማት ጋርም እንደምትመክር አስረድተዋል። ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳይጎዳ የሚያደርግ ርምጃም ትወስዳለች ብለዋል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ነገር አትታገስም ሲሉ አብራርተዋል።
በሊባኖስ ያለው አለመረጋጋት ወደባሰ ቀውስ የሚሄድ ከኾነ በሚል በሀገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ችግር እንዳያጋጥማቸው ለማገዝ ኮሚቴ ስለመቋቋሙም ነው ያብራሩት። 120 ሺህ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ስለሚገኙ ችግር እንዳያጋጥማቸው ቅድመ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል። ኢትዮጵያውያኑ ያፈሩት ንብረት ችግር እንዳይገጥመው ኮሚቴው እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!