“1 እና 0” የኮምፒውተር ዓለም ቁልፍ ቁጥሮች

34

ባሕር ዳር: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዕለት ከዕለት ሕይዎታችን ውስጥ ያሉብንን የሥራ ጫናዎች በማቅላል እና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ኮምፒውተር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም ግሩም ነው። ኮምፒውተር ጊዜን፣ ጉልበትን እና ሃብትን በመቆጠብ ሕይዎትን አቅልሏል። በተለያዩ አገልግሎቶች የደንበኞች እርካታ እንዲጨምር የላቀ ሚናን እየተጫወተም ይገኛል።

መረጃ እጅግ በበዛበት ዓለም እየኖርን ሕይዎትን ያለ ኮምፒውተር ስናስብ ደግሞ ጠቀሜታው ጎልቶ ይታየናል። ከኮምፒውተር የምንፈልገው አገልግሎት በሦስት ሂደቶት የሚያልፍ ነው። እነዚህም ጥሬ መረጃ መስጠት (Inputting)፣ የቅንብር ሂደት (Processing) እና ውጤት ማመንጨት (outputting) ናቸው።

ኮምፒውተር ከሚተገበረው ነገር በመነሳት ሁሉንም ነገር መረዳት እና መተንተን የሚችል ማሽን አድርገን እናስበዋለን። ነገር ግን መረዳት የሚችለው አንድ እና ዜሮ ቁጥሮችን ብቻ ነው። “1 እና 0” በማቀናበር ለኮምፒውተሩ ‘ኦን’ (on) እና ‘ኦፍ’ (off) የሚባሉ የኤሌክትሪክ ሞገዶችን በመላክ ነው ተግባራትን የሚሠራልን። “1 እና 0” የሚጠቀመው የቁጥር ሥርዓት “ባይናሪ” ይባላል።

ባይናሪ የሚባለው የቁጥር ሥርዓት በ17ኛው ክፍለ ዘመን በጎትፍራይድ ሌብኒዝ የተፈጠረ ነው፡፡ በሒሳብ እና በኮምፒውተሩ ዓለም ባይናሪ ወይም ቢት የዳታ ትንሹ ንዑስ ክፍል ነው። ኮምፒውተር ላይ የኤሌክትሪክ ሞገዶች በ ዜሮ እና በአንድ የሚወከሉ ናቸው። 0 ሁልጊዜም ‘ኦፍ’ ሞገድን የሚወክል ሲኾን 1 ደግሞ ‘ኦን’ ን ይወክላል። በመኾኑም ሁሉም መረጃዎች በእነዚህ ቁጥሮች ቅንብር ተወክለው ኮምፒውተሩ ወደ ሚረዳው ውከላ ይቀየራሉ።

ማንኛውም በዜሮ እና በአንድ የሚወከል ቁጥር ደግሞ ባይናሪ ቁጥር ይባላል። በየትኛውም ኮምፒውተር የሚቀናበር መረጃ በሁለቱ ቁጥሮች ካልተወከለ በስተቀር የምንፈልገውን አገልግሎት ማግኘት አንችልም። ስለዚህ ለኮምፒውተራችን የምንሰጠው ምልክት ወደ ባይናሪ ከተቀየረ በኋላ ነው በምንፈልገው መንገድ በስክሪን ላይ ውጤቱን ማየት የምንችለው።

ለየትኛውም ዓይነት የኮምፒውተር ሥርዓት እና ተግባራት እንደ ጀርባ አጥንት የሚቆጠረው 0 እና 1 ውከላ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይሰጠናል። ድረ ገጽ ላይ መረጃን ከተቀመጠበት ቋት አውጥቶ ለመመልከት፣ ፋይል ለመፍጠር እና ለውጦችን ለማድረግ፣ የግራፊክስ መረጃዎችን ለመመልከት፣ የሒሳብ ቀመሮችን እና የዳታ ትንተናን ለመሥራት ይጠቅመናል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በታላቅ ቦታ፣ የታላቅ ሰው ስም በሚዘከርበት ስፍራ አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ ትርጉሙ ዕልፍ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ጋር በተርኪየ የምታደርገው ድርድር ወሳኝ መሻሻሎች የተገኘበት መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡