
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአሜሪካ ችካጎ ግዛት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በብዛት እየሞቱ ያሉት ጥቁሮች መሆናቸው ተገለጸ፡፡ የችካጎ የጤና ኃላፊዎችን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ከአጠቃላይ የችካጎ ሕዝብ ጥቁሮች 30 በመቶ ቢሆኑም በኮሮና ቫይረስ ከሞቱት ግን 70 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡
ዴትሮይት፣ ሚልዋኪ፣ ኒው ኦርሊያንስ እና ኒውዮርክም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጥቁሮች የሚገኙባው ከተሞች ናቸው፤ በእነዚህ ከተሞች የኮሮና ሥርጭት እየሰፋ መሄድ ደግሞ ሌላ ሥጋት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በአሜሪካ በአጠቃላይ ከ370 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የዘገበው ቢቢሲ የሟቾች ቁጥር 11 ሺህ መድረሱንም አስታውቋል፡፡
ከቀናት በፊት በችካጎ 6 ሺህ 680 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 824 ጥቁሮች ናቸው፡፡ ባለፈው እሑድ በችካጎ 98 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ ከእነዚህ ውስጥ 71 ሟቾች ጥቁሮች ናቸው፡፡
ዝርዝር ምክንያቱ የተጠና ባይሆንም በዘገባው የተመላከተው ‘‘የጥቁሮች አማካይ የዕድሜ ጣሪያ ከነጮቹ ያነሰ ስለሆነ ነው’’ የሚል ነው፡፡
አካላዊ መራራቅ፣ እጆችን አዘውትሮ መታጠብ፣ ሲስሉና ሲያነጥሱ አፍና አፍንጫን በመሀረብ ወይም በፊት መሸፈኛ ጭምብል በማፈን የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ይቻላል፡፡
በአብርሃም በዕውቀት